ኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት አገራዊ ዕውቀትን መጠቀም አለባቸው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት አገራዊ ዕውቀትን መጠቀም አለባቸው
አዲስ አበባ የካቲት 21/2011ኢትዮጵያውያን አንድነትና አብሮነታቸውን ጠብቀው ለማቆየት አገራዊ ዕውቀትን መጠቀም እንዳለባቸው የታሪክ ምሁራን ገለጹ።
''አድዋ የሰውነት ማህተም'' በሚል መሪ ሃሳብ የአድዋን ታሪክ ለመዘከር ከየካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው የክብረ አድዋ አካል የሆነው ጉባኤ ዛሬ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ተካሄዷል።
የደራሼ ብሔረሰብ የባህል ቡድንም ለመድረኩ ሙዚቃዊ ትርዒት አቅርቧል።
በጉባዔው ላይ የታሪክ ምሁራን የአድዋን ታሪክ የተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበው ውይይት ተካሄዶበታል።
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሐሰን ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ ለቀረቡት ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ፤ "አገራዊ ዕውቀትን በአግባቡ በመጠቀም የአገሪቷን አብሮነትና አንድነት ማስጠበቅ ያስፈልጋል"።
ከውጭ በተዋስናቸው ዕውቀቶች ላይ ከመንጠልጠል በገዳማትና በመስኪዶች የሚገኙ አገር በቀል ዕውቀቶችን መጠቀም ጥቅሙ ከፍተኛ እንደሆነም አስረድተዋል።
ኢትዮጵያ በምንም ነገር የማትጠፋ አገር መሆኗን ታሪክም ሆነ ሃይማኖት እንደሚገልጹ የተናገሩት ዶክተር አህመድ ህጻናትንና የዕውቀቱ ማህደር የሆኑትን ሽማግሌዎችን ማክበር እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ሌላው በመድረኩ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡት የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልማው ተክሌ ዛሬ ከትናንት ትምህርት በመውሰድ ነገውን ብሩህ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በመሆኑም በኢትዮጵያውያን አብሮነት ላይ ለመስራት ታሪክ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባም ተናግረዋል።
መሪዎች መልካምና ክፉ ነገር ሰርተው እንደሚያልፉ ያስታወሱት ዶክተር አልማው፤ "ትንንሽ ነገሮች ይዞ በመካረር አደባባይ ላይ ድንጋይ ይዞ መውጣት የሚጎዳ" ተግባር ስለመሆኑም አብራርተዋል።
የመድረኩ አወያይ የነበሩት የታሪክ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ ኢትዮጵያን ለመበታተን የሚሰሩ ሃይሎችን መቋቋም የሚቻለው ከድህነት፣ ከድንቁርናና ከበሽታ መውጣት ሲቻል በመሆኑ በስፋት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
እርስ በርስ መወነጃጀሉ ከድህነት የማያወጣ መንገድ በመሆኑ በመከባበር ከድህነት ለመውጣት ጥረት ማድረግ ተገቢ እንደሆነም ገልጸዋል።
አገራዊ አንድነትን ማጠናከር የሚቻለው ህጻናትና አዋቂዎችን በማክበር እንደሆነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
''አድዋ የሰውነት ማህተም'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚከናወነው ክብረ አድዋ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲና የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በመተባበር ያዘጋጁት ሲሆን በተለያዩ ዝግጅቶች እስከ የካቲት 23 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ የሚካሄድ ነው።