የሐረሪ ክልል አመራር በግብር አሰባሰብ የሚታዩትን ጉድለቶችን ለማስተካከል መሥራት አለበት ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
የሐረሪ ክልል አመራር በግብር አሰባሰብ የሚታዩትን ጉድለቶችን ለማስተካከል መሥራት አለበት ተባለ
ሐረር የካቲት 21/2011 በሐረሪ ክልል በየደረጃው ያለው አመራር በግብር አሰባሰብ የሚታዩትን ጉድለቶችን ለማስተካከል ሕዝቡን ያሳተፈ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለበት የክልል ርዕሰ መስተዳድሩ አስገነዘቡ።
በክልሉ ሁሉንም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ያካተተ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።
ርዕሰ መስተዳድሩ አቶ ኦርዲን በድሪ በግብር ጉዳይ ላይ በመከረው ስብሰባ ላይ እንዳሳሰቡት አመራሩ እስከ ወረዳ ድረስ የሚዘልቅ የሕዝብ ንቅናቄ መድረኮችን በመፍጠር ጉድለቶችን ማረም ይጠበቅበታል።
በዚህም የንግዱ ማህበረሰብ ግብሩን አምኖበት እንዲከፍል ማድረግና የባለቤትነት ስሜት መፍጠር ይገባል ብለዋል።
በክልሉ ባለፉት ስድስት ወራት የተሰበሰበው 62 በመቶ መሆኑ አንዱ ማሳያ ለዚሁ አንዱ እንደሆነም ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።
''የሕግ የበላይነት አለመከበር በገቢ አሰባሰብ ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል'' ያሉት አቶ ኦርዲን፣ለዚህም ሕገ ወጥ ንግድና የገንዘብ ልውውጥን መስፋፋትን ዋነኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ አብራርተዋል።
የሐረር ከተማ መዘጋጃ ቤቱ ሹም አቶ አሪፍ መሐመድ እንዳሉት የክልሉን ገቢ ለማሳደግ የሕግ የበላይነትን ከማስከበር ጎን ለጎን ባለሀብቶችን በመሳብና የግብር ከፋዮችን ቁጥር መጨመር ያስፈልጋል።
እንዲሁም በከተማው በሕገ ወጥ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎችን ወደ ሕጋዊነት ማምጣት ያሻል ብለዋል ።
የክልሉ ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰሚራ ሐጂ ዩሱፍ አመራሩ በተቀናጀና በባለቤትነት ስሜት በመንቀሳቀስ ለገቢ አሰባሰብ ትኩረት መስጠት እንጂ፤ እንደ ተጨማሪ ሥራ አድርጎ መውሰድ እንደማይገባው አስረድተዋል።
በስብሰባው ከሁሉም ሴክተር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣና በግብር አሰባሰብ ላይ የሚታዩ ችግሮችን ለማቃለል የሚሰራ ግብረ ኃይል ተቋቁሟል።
ግብረ ኃይሉ በ60 ቀናት ውስጥ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመሙላትና ግብር ከፋዩ ግዴታውን እንዲወጣ ለማድረግ ይሰራል።
በሐረሪ ክልል 14ሺህ የሚጠጉ ግብር ከፋዮች ይገኛሉ።