የዓድዋ ድል ታሪክን የሚዘክር ሙዚየምና ቤተመጻፍት ሊሰራለት እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ - ኢዜአ አማርኛ
የዓድዋ ድል ታሪክን የሚዘክር ሙዚየምና ቤተመጻፍት ሊሰራለት እንደሚገባ ምሁራን አመለከቱ
አክሱም የካቲት 21/2011 የአለም ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ተጋድሎ የሆነውን የዓድዋ ድል ታሪክ የሚዘክር ሙዚየምና ቤተመጻፍት ሊሰራለት እንደሚገባ በአክሱም ዩኒቨርስቲ የታሪክ ምሁራን አመለከቱ።
ምሁራኑ እንዳሉት ዘመን ተሻጋሪው የአድዋ ድል ታሪክ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ሁሉም የበኩሉን መወጣት አለበት፡፡
በዩኒቨርስቲው የታሪክ ምሁር ዮርዳኖስ ሙሉጌታ የዓድዋን በዓል ምክንያት በማድረግ በሰጡት አስተያየት የዓድዋ ድል ከታሪካዊነቱ አንጻር ተገቢውን ትኩረት እንዳልተሰጠው ተናግረዋል፡፡
"በዓመት አንዴ ከማክበር ባሻገር ትክክለኛውን ታሪክ ተጽፎና ተሰንዶ ለቱሪስት መስህብነት ጥቅም ላይ እንዲውል መደረግ አለበት" ብለዋል።
የዓድዋ ድል ትልቅ የዓለም ቅርስ መሆኑን ያመለከቱት ምሁሩ ድሉን የሚዘከር ዘመናዊ ሙዚየምና ቤተመሓህፍት ሊሰራለት እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
የድሉን ደማቅ ታሪክ እንዲጻፍ ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡም ጠቁመዋል።
"የዓድዋ ድል የአለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት መሰረት በመሆኑ ኢትዮጰያዊያን ልዩነታችን በማጥበብና አንድነታችንን በማጠናከር ለሃገራችን እድገት መስራት ይጠበቅብናል "ብለዋል።
በዩኒቨርሲቲው የታሪክና ቅርስ አስተዳደር መምህር ግርማይ ሓለፎም በበኩላቸው፣በአድዋ ጦርነት ትልቅ ጀግንነትና መልካም ስራ ሰርተው የለፉ ግን ታሪካቸውን ያልተነገረላቸውና ያልተጻፈላቸው ማስታወስ ተገቢነት እንዳለው ገልጸዋል።
በወቅት መላው የኢትዮጵያዊያን እንደተሳተፉ አስታውሰው "በተለይ ወራሪው ኃይል እንዲሸነፍ የእነ ባሻይ አውዓሎም ፣የእነ ጀነራል አሉላ አባነጋ፣ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ፣የእነ ራስ መንገሻ ዮሐንስ ፣ፊት አውራሪ ገበየሁ እና ንጉስ ተክለሃይማኖት የታሪክ ስራዎች ዘመን የማይሽረው ደማቅ የታሪክ ክስተት ነው" ብለዋል።
እነዚህና ሌሎች ጀግኖች በአድዋ ጦርነት ድል ላይ የነበራቸው አስተዋጽኦ እስካሁን በአግባቡ እንዳልተጻፈላቸው ነው መምህር ግርማይ የተናገሩት፡፡
በቀጣይም የታሪክ ምሁራን ኢትዮጵያውያንን የሚያቀራርብ ታሪኮችን በመጻፍና በማደራጀት እንዲሁም ጥናትና ምርምር በማካሄድ የአድዋ ድልን ለትውልድ እንዲተላለፍና ለቱሪዝም ልማት እንዲውል የድርሻቸውን መወጣት እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ታሪክን ለፖለቲካ ፍጆታና ለአንድ ወገን ሲያዳሉ ሳይሆኑ የኢትዮጵያወያንን ትክክለኛ ገድል ተጽፎ ሙያዊ ትንታኔ በማስቀመጥ ለቀጣይ ትውልድ ማስተማር እንደሚገባ ጠቁመዋል።