የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለ10 ዓመት የሚመራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ - ኢዜአ አማርኛ
የኮንስትራክሽን ዘርፉን ለ10 ዓመት የሚመራ ፍኖተ ካርታ ተዘጋጀ
አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 በኮንስትራክሽን ዘርፍ ያለዉን ችግር የሚፈታና ለ10 ዓመታት የሚያገለግል ፍኖተ ካርታ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
4ኛዉን ሀገር አቀፍ የትምህርት ስልጠና፤ የምርምርና የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትስስር ለመፍጠር “የዘመነ ኮንስትራክሽን እና ቅንጅታዊ አሰራር ለዘላቂ ሀገራዊ ልማት” በሚል መሪ ሐሳብ ዛሬ ውይይት ተደርጓል።
በውይይቱም በዩኒቨርሲቲዎች በቴክኖሎጂ ዲፓርትመንት ያሉ ኃላፊዎች፤ የክልል የኮንስትራክሽን ዘርፍ ኃላፊዎች፣ የምርምር ተቋማትና የግል የኮንስትራክሽን ድርጅቶች ተካፍለዋል።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ኃላፊ ዶክተር አርጋዉ አሻ ፍኖተ ካርታው ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር በመፍጠርና ጥናትና ምርምር በማድረግ ከውጭ ሀገር የሚገቡትን ቁሳቁሶች በሃገር ውስጥ ለማምረት ያስችላል ብለዋል።
በኮንስትራክሽን አስተዳደር ያለውን ችግር ለማስቀረት፣ የምክር አገልግሎት ለመስጠት፣ ተማሪዎች ወደ ስራ ዓለም ሲመጡ እንዳይቸገሩ ተግባር ተኮር ትምህርት ለመስጠት፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ለማከናወንና ፕሮጀክቶች ተጀምረዉ እስኪያልቁ በተቀናጀ መልኩ ለመስራት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢንስቲትዩቱ የቴክኖሎጂ ሽግግር ባለሙያ ወይዘሮ ፋናኤል ንጉሴ ፍኖተ ካርታዉ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ትስስር ፈጥርን ለምንሰራቸው ስራዎች አቅጣጫ የሚያሳይና በዩኒቨርሲቲዎች የሚደጋገሙ ጥናቶችን በማሰቀረት የገንዘብና የጊዜ ብክነትን ያስቀራል ብለዋል።
ምርጥ ተሞክሮ ያላቸዉ ባለሙያዎች የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲያደርጉም የትስስሩ ዋነኛ ተግባር ነው ብለዋል።
ፍኖተ ካርታው ላለፉት ሁለት ዓመታት የኮንስትራክሽን ዘርፉን የተሻለና ውጤታማ ለማድረግ ሲዘጋጅ መቆየቱ ተገልጿል።