የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ

አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ለማድረግ ዛሬ አዲስ አበባ ይገባሉ።

ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ በሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር በሁለትዮሽና በቀጠናዊ ጉዳዮች ውይይት እንደሚያደርጉ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

በተጨማሪም በኢትዮጵያና በኬንያ መካከል ያለውን የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን የበለጠ ለማጠናከር ዓላማ አድርጎ ዛሬ በሚካሄደው የኢትዮ-ኬንያ ንግድና ኢንቨስትመንት ፎረም ላይ ይሳተፋሉ ተብሏል።

በዚህ ፎረም ላይ ለመሳተፍም ቁጥራቸው 100 የሚደርሱ የኬንያ መንግስት ባለስልጣናት፣ የኮርፖሬትና የንግድ ማህበረሰብ ተወካዮች ከፕሬዝዳንት ኡሁሩ ጋር ወደ አዲስ አበባ እንደሚመጡ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ እና ኬንያ ታሪካዊና ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንኙነት አላቸው።

ሁለቱ አገሮች በ1946 ዓ.ም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በ1953 ዓ.ም ኤምባሲዋን በናይሮቢ ከፍታለች።

በተመሳሳይ ኬንያ በ1959 ዓ.ም ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ የከፈተች ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በርካታ የሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር በመስራት ላይ እንደሚገኙ የጽህፈት ቤቱ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም