ባለ ራዕዩ ወጣት

160
አስማረች አያሌው /ኢዜአ / ወጣት ዮናስ ሸዋንግዛው ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ወሎ ሰፈር አካባቢ ነው፤በልጅነቱ እንደ ማንኛውም ህፃን ከጓደኞቹ ጋር የሽቦ መኪና እየሰራ ይጫወት  እንደነበር ያስታውሳል፤በታዳጊነት ዘመኑም ዲስኮ ሰአት እየፈታና እየገጣጠመ  የተበላሹ ኤሌክትሮኒክስ እቃዎችንም ለመጠገን ሙከራ ያደርግ እንደነበር ይናገራል ፡፡ ቀስ በቀስ የቴክኒክ ሙያን እየወደደ የመጣው ዮናስ ከትምህርቱ በተጓዳኝ ክህሎቱን ሊያሳድግበት የሚችል ጋራዥ በመግባት መሰረታዊ የብረታብረት ስራን በሳምንት 20 ብር እየተከፈለው እንደለመደ ነው የሚገልፀው፡፡ “ስራ መፍታት አልወድም “ የሚለው ዮናስ ስራ ባገኘበት ቦታ ሁሉ  የብረታ ብረት ፣የእንጨት ስራ እንዲሁም ጋራዥ ውስጥ የመኪና ጥገናም ይሰራ ነበር ፤ከስራ በተጓዳኝ በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ “ሰው እቃ ተበላሸብኝ ብሎ ሲያሳየኝ ማሽኑን ከመስራት ባሻገር፣ እንዴት ነው የተሰራው የሚለውን ሚስጥር ለማወቅ እጥራለሁ እየለካሁም እንደ መረጃ የማስቀመጥ ልምድ አለኝ ” ብሏል፡፡ “ችሎታዬን የተመለከተ ጓደኛዬ በ2004 ዓም በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅቼ እንድሰራ መከረኝ፣እኔም አስፈላጊውን ሁኔታ አሟልቼ የራሴን ስራ ጀመርኩ “ የሚለው ዮናስ ስራውን በ10ሺህ ብር መነሻ በመኖሪያ ቤቱ የብረታብረት ስራ ኢንተርፕራይዝን በማቋቋም   በርና መስኮት ማምረት እንደጀመረ ያስታውሳል፡፡ የስራውን ውጤታማነት የተመለከቱ  የወረዳ አመራሮችም ስራ ከጀመረ ከስድስት ወራት በኋላ የመስሪያ ቦታ እንዳመቻቹለትም ይገልፃል፡፡ በስራው ምን ለውጥ አገኘ ? “የበርና መስኮት ስራ ላይ መቆየት አልፈለኩም ፣ስራው ተመሳሳይነት ስላለው ጭንቅላት የማይፈትን  ሆነብኝ” የሚለው ዮናስ የቴክኒክ ደረጃው ከፍ ወደ አለ ማሽን ወደ ማምረት ስራ መግባቱን ያስረዳል፡፡ ሰዎችን ሲጠይቅ  ከቡና ጋር የተያያዙ ስራዎችን በማግኘቱ የደረቅ ቡና መቀሸሪያ፣የእሸት ቡና መፈልፈያ፣የቡና  መቁያ እንዲሁም የቅመማ ቅመም ማሽነሪዎች የጥራጥሬ ማበጠሪያ መፈልፈያና መፈተጊያ ማሽኖች ከሰራቸው መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ “የቴክኒክ ሙያ ገደብ የለውም፣ቴክኒክ ከታወቀ ስራው ውስን አይሆንም ፣ምን ቢደረግ ምን ውጤት ያመጣል “የሚለውን በመሞከር ስራውን አስፍቶ እንደሄደ ነው የሚገልፀው፡፡ ከቡና ስራ ጋር በተያያዘ አብዛኞቹ ደንበኞቹ በክልል የሚገኙ ቡና አምራቾች እንደሆኑ የገለፀው ዮናስ በወለጋ ፣ቴፒ፣ሻኪሶና እንዲሁም በአዲስ አበባ ደግሞ የኦሮሚያ ቡና አብቃይ  ህብረት ስራ ዩኒየን የቡና  መቁያ ማሽኑን እየተጠቀመበት መሆኑን አሰረድቷል፡፡ የበለጸጉ አገሮች ተጠቅመውባቸው ውጤታማ የሆኑባቸውና በነፃ ለታዳጊ አገሮች የለቀቋቸውን አዋጪና ችግር ፈቺ ቴክኖሎጂዎችን ቀድቶ በመጠቀም የሕብረተሰቡን ፍላጎቶች መሰረት ያደረጉ ችግር ፈቺ የፈጠራ ውጤቶችን ማፍለቅ አይነተኛ ሚና አላቸው፡፡ በዚህም እስከ አሁን  የተለያዩ ሃያ ማሽኖችን ለአገልግሎት እንዳበቃ የተናገረው ዮናስ  የቡና ማድረቂያ ማሽን  ከኤንተርኔት ሞዴሉን በመቅዳት እየሰራ እንደሆነ ጠቅሶ በስራ ሄደት የሚያጋጥመውን የቴክኒክ እክል “እንደ እንቅፋት አልቆጥረውም ይልቁንም እየተማርኩበትም እሄዳለሁ ፤ችግሩ ሲፈታ ደግሞ ስኬት ይሆናል “ ብሏል፡፡ ማሽኑ ከምን ይሰራል ፤ያመጣው ውጤትስ ? ከውጪ የሚገቡት የቡና መቀሸሪያና የእሸት ቡና መፈልፈያ ማሽኖች እስከ 2 ሚሊየን ብር እንደሚገመቱ የገለፀው ዮናስ በሃገር ውስጥ እንደ ማሽኑ መጠን እስከ 300 ሺህ ብር በሚደርስ ወጪ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ነው የገለፀው፡፡ ማሽኖችን በሃገር ውስጥ መስራቱ ለሃገር ጠቀሜታው የጎላ እንደሆነና "የውጪ ምንዛሬን ለማስቀረት እንሰራለን፣በብልሽት ወቅትም የመለዋወጫ ችግር አያጋጥመንም” ብሏል፡፡ ከውስን ቴክኖሎጂዎች በስተቀር ሃገር ውስጥ የሚገኙ ብረቶችን ቆራርጠውና ቅርፅ አውጥተው ወደ ማሽነሪነት እንደሚቀይሩና እንደ ሻፍት፣ዲናሞ፣ሞተር እና ስፖርቶ የመሳሰሉት እቃዎች ግን ከውጪ የሚገቡ መሆኑን ነው የገለፀው ዮናስ፡፡ “የቴክኒክ ሙያ የተገደበ አይደለም እኔም መገደብ አልወድም” ያለው ወጣቱ በቡናው ዘርፍ ከሚሰራቸው ማሽኖች በተጓዳኝ በደንበኞች ጥያቄ የብሎኬትና የቴራዞ ማምረቻ ማሽኖችን መስራቱን ገልጿል፡፡ አሁን ላይ ትላልቅ ማሽኖችን በመጠቀም ማሽኖቹን እንደሚያመርት የገለፀው ወጣቱ “ሁሌም ወደ ተሻሉ ቴክኖሎጂዎች ለመሸጋገር” እንደሚያልም ነው ያስታወቀው፡፡ ስለ መንግስታዊ ድጋፎች ምን ይላል ? ከመንግስት ያገኘው ሼድ ለስራ መነሻነት እንደጠቀመው የተናገረው  ወጣቱ ከውጪ የሚገቡ ማሽነሪዎችን ተክተው የሚያመርቱ ኢንተርፕራይዞችን ይበልጥ መደገፍ እንደሚገባ ነው የገለፀው፡፡ “ዘርፉን ለማበረታታት ሼድ መስጠቱ ብቻ በቂ አይደለም” ያለው ዮናስ  ይልቁንም መንግስት ከውጪ የሚገቡትን ማሽነሪዎች መቅዳት እንዲችሉ ሁኔታዎችን ማመቻቸት አለበት ባይ ነው፡፡ በተጨማሪም በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በመንግስት ተቋማት እንዲሁም በአእምሮ ንብረትነት ተመዝግበው የተቀመጡ ዶክመንቶች ወደ መሬት ወርደው ሊተገበሩ  ይገባልም ብሏል፡፡ እንዲሁም በየተቋማቱ በብልሽት ያለአገልግሎት የተቀመጡ ማሽነሪዎች ዝንባሌ ያላቸው ወጣቶች እየፈታቱ እንዲማሩባቸው ሊደረግም ይገባል፡፡ ቆሻሻ ማንሻ መኪና ላይ የሚገጠም ኮምፓክት ማሽን ለመስራት በዝግጅት ላይ መሆኑን  የገለፀው ወጣቱ “በቅርበት የማይገኙ እቃዎችን መንግስት ሊያግዘኝ ይገባል" ሲል አሰተያየቱን ሰጥቷል፡፡ ከውጪ ሲገባ እስከ ሶስት ሚሊየን የሚገመተውን የቆሻሻ ማንሻ መኪና በሃገር ውስጥ ኮምፓክት ማሽኑን በብዛት ማምረት ከተቻለ የቆሻሻ መዝረክረክን መቀነስ እንደሚቻል ነው የገለፀው፡፡ ስራን ባህል ስለማድረግ ምን አለ ? “ስራን ከወደድን የወደፊት ህይወታችንን እንወደዋለን፣ካልሆነ እጃችንን ከታች ይሆናል” ያለው ዮናስ አብዛኛው የሃገራችን ወጣት  ዝቅተኛ ገቢ ካለው ህብረተሰብ የተገኘ በመሆኑ “ድህነት እዚህ ጋ ይብቃ ማለት አለበት፤ሲሰራም  ነው ድህነትን ማስቆም የሚችለው” ብሏል፡፡ የምንሰራውን ስራ ከወደድነው ትልቅ ለውጥና እርካታ አለው ያለው ወጣቱ “ስራን ባህል ካደረግን በምንሰራው ስራ እንኳን ባንደሰት ለምንወደው ስራ ያንደረድረናል” “ድህነትን መጥላትና አሜን ብለን መቀበል የለብንም ” የሚለው ዮናስ ስኬት የሚገኘው  እንደ ዱብ እዳ ሳይሆን በትጋት ነው ብሏል፡፡ በስራ መለወጥ ማለት በፋይናንስና በአስተሳሰብ ማደግ መሆኑንም ሳይገልጽ አላለፈም ፡፡ የት ለመድረስ ያልማል ? “ኢትዮጵያ በቴክኒክ ዙሪያ በጣም አድጋ ፍፁም ወደ ሆነ የቴክኒክ ብቃት ላይ ደርሳ ማየት ህልሜ ነው” ያለው ዮናስ ከግዙፍ የመድሃኒት ማምረቻ ቀላል ቴክኖሎጂን እስከሚጠይቁ ምርቶች ከሌሎች ጋር ተዋህደን ወደ ዲጂታል ማሳደግ ይኖርብናል ብሏል፤በቅጥቀጣና በብየዳ የሚከናወኑ ስራዎችን የራሳችንን ሮቦቶች ሰርተን በወርክሾቦች ማሰማራትንም አልማለሁ ”ይህ እንዲሆንም ተስፋ ሰጪ ሙከራዎች ይታዩኛል” ብሏል፡፡ “በሃገር ውስጥ  ገበያ ብቻ ተወስኜ መቅረትን አልፈልግም” የሚለው ዮናስ በተለይ ቡና አምራች ከሆኑ የአፍሪካ ሃገራት ጋር ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልጿል፡፡ አሁን ላይ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ካፒታል ያንቀሳቀሳል፣ ትላልቅ የማምረቻ ማሽኖች አሉት ለ18 ሰዎችም ቋሚና ጊዜያዊ  የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ የስራ እድል የተፈጠረላቸው ወጣቶች ምን ይላሉ ? ወጣት አይዳ በቀለ በድርጅቱ ወስጥ ረዳት የሂሳብ ሰራተኛ ሆና ታገለግላለች ፤በወር 1 ሺህ አምስት መቶ ብር የሚከፈላት ሲሆን በተጓዳኝ ሙያ እየለመደች መሆኑን ተናግራለች፡፡ “መሰልድርጅቶች መበራከታቸው የስራ እድልን ይፈጥራሉ” ያለችው አይዳ በተለይ ወቅታዊ ስራ ሲያጋጥም  ብዙ ሰዎች እንደሚቀጠሩ ተናግራለች፡፡ ሌላው ወጣት ሚኪያስ ታደሰ በኢንተርፕራይዙ የቶርኖ ስራዎችን እንደሚያመርት ገልፆ በየቀኑ አዳዲስ ክህሎት እና የተለየ እውቀትን ከማግኘት ባሻገር በወር 6ሺህ ብር  እንደሚከፈለው ጠቁሟል፡፡ በስራው ለማሽኖቹ ግብአት የሚሆኑ የተለያዩ ቁሶችን እንደሚያመርትና ገበያ ላይ የማይገኙ እቃዎችንም አመሳስሎ በሞደፊክ እንደሚሰራ ነው የተናገረው፡፡ ኢንተርፕራይዞችን የሚደግፈው ተቋም  ምን ይላል ? በፌደራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ልማት ኤጀንሲ የቴክኖሎጂ ዲዛይን ከፍተኛ ሜካኒካል መሃንዲስ አቶ መሀመድ ነጋሽ እንደተናገሩት ኤጀንሲው ቴክኖሎጂዎችን ፕሮቶታይፕ(ናሙና)  በመስራት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጥቅም ላይ እንዲውሉ የማሸጋገሩን ተግባር እያከናወነ መሆኑን ይገልፃሉ፡፡ ከተሰሩትም መካከል የሽመና ማሽኖች ፣የሻማ ማምረቻ፣ የቆጮ መፋቂያና የሸክላ መስሪያ ማሽኖች ይገኙበታል ብለዋል፡፡ ሃሳባቸው ጥቅም ኖሮት የሚተገብሩበት አቅም  ያጡ የፈጠራ ባለሙያዎች የኤጀንሲውን ወርክሾፕ በተመጣጣኝ ዋጋ መገልገል እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡ እንዲሁም ማሽን አምራች ኢንተርፕራይዞች ከአቅማቸው በላይ የሆኑ ቴክኖሎጂዎችና እገዛ ሲያስፈልጋቸው ኤጀንሲው ለመተባበር ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡           
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም