የኤሌክትሪክ መቆራረጥን በአንድ ማዕከል ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ መቆራረጥን በአንድ ማዕከል ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊደረግ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 የኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት በተደጋጋሚ የሚከሰተውን የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ችግር ለማቃለል በአንድ ማዕከል ሆኖ ለመቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ተግባራዊ ሊያደርግ መሆኑን አስታወቀ።
የአገልግሎቱ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ መላኩ ታዬ ለኢዜአ እንደገለጹት የኤሌክትሪክ ሃይል ስርጭትን በአንድ ማዕከል ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ ለመጠቀም የሚያስችል ስራ 81 በመቶ ተጠናቋል።
በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስራው ተግባራዊ እንደሚሆንና የኤሌክትሪክ ኔትወርክ ማሻሻያ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በመሰረተ ልማት ያለመዘመን፣ ሃይል ቆጣቢ መሳሪያዎችን ባለመጠቀምና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች 21 በመቶ የሚሆነው ሃይል ለተጠቃሚው ሳይደርስ ይባክናል።
ይህን ያህል የኤሌክትሪክ ኃይል ለተጠቃሚው ሳይደርስ መቅረቱ የአቅርቦቱ መጠን ከ25 በመቶ ላልደረሰው አገልግሎት ኪሳራ መሆኑም ነው የሚነገረው።
አገሪቷ ላለፉት ዓመታት ኤሌክትሪክ ለማምረት ባከናወነችው ተግባር በአስር እጥፍ ማቅረብ ብትችልም የተመረተውን ምርት ለህብረተሰቡ ለማድረስ የሚያስችል የመሰረተ ልማት ግንባታ ያለመከናወኑ ለሃይል ብክነት ዳርጎታል።
ይሁን እንጂ አገልግሎቱ እነዚህን ችግሮች በመገምገም የኤሌክትሪክ ስርጭቱን በአንድ ማዕከል ሆኖ መቆጣጠር የሚያስችል አዲስ ቴክኖሎጂ ለመጠቀም በመንቀሳቀስ ላይ መሆኑን አቶ መላኩ ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የሚያስችል የሰው ሃይል ስልጠና፣ አዳዲስ የሰው ሃይል ቅጥርና ሌሎች ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላት ላይ መሆኑን አመልክተው በቀጣይ አንድ ወር ውስጥም መተግበር ይጀምራል ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ያረጁ ኔቶርኮችንና ፖሎችን ለመተካት በስምንት ዋና ዋና ከተሞች የተጀመረው ስራ 98 በመቶ ተከናውኗል።
ዘርፉ ለመልካም አስተዳደር ግድፈት ተጋላጭ መሆኑን በመረዳትም በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ የነበሩ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን ገምግሞ የመልካም አስተዳደር ቸግር በፈፀሙ ሰራተኞች ላይ የእርምት እርምጃ መውሰዱንም አስታውቀዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በቀጣይ ተመሳሳይ ቸግሮች እንዳይፈጠሩም ለሁሉም ሰራተኛ በየደረጃው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና መሰጠቱንም አቶ መላኩ ተናግረዋል።