ቀጥታ፡

አብይ ጾምን ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት ፣ ነዳያን በመመገብና በማልበስ ማሳለፍ እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 የአብይ-ጾምን ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ነዳያንን በመመገብ እና በማልበስ ማሳለፍ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን አሳሰበች።

የቤተክርስቲያኑዋ ፓትርያርክ ብጹ አቡነ ማቲያስ የፊታችን የካቲት 25 ቀን 2011 ዓ.ም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚጀመረውን አብይ-ጾም አስመልክቶ ቃለ ቡራኬ አስተላልፈዋል።

በቃለ ቡራኬያቸውም ህዝብ ክርስቲያኑ ወርሃ ጾሙን ከምንም በላይ ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት፣ ነዳያን በመመገብና የታረዙ ወገኖቹን በማልበስ ማሳለፍ ይገባናል ነው ያሉት።

"በሚጠፋ ነገር ከምንጠፋፋ የማይጠፉትን መንፈሳዊ መሳሪያዎችን ጨብጠን በህይወት መኖርን ምርጫችን ብናደርግ ከጥበበኞች ሁሉ የምንበልጥ ጥበበኞች እንሆናለንም" ብለዋል።

"ለመጪው ሕይወት ብቻ ሳይሆን አሁን ላለንበት ጊዜያዊ ሕይወትም ቢሆን ከመለያየት ይልቅ አንድነትን፣ ከጥል ይልቅ ፍቅርን፣ ከቁጣ ይልቅ ትዕግስትን፣ ከርኩሰት ይልቅ ቅድስና እንደሚበልጥም "ተናግረዋል።

በተጨማሪም ከመግደል ይልቅ ማዳንን፣ ከአድመኝነት ይልቅ ሠላምን እንዲሁም ከስካር ይልቅ ራስ መግዛት እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት።

ጾም ማለት ፈቃደ ሥጋን ትተን ለፈቃደ ነፍሳችን ብቻ የምንታዘዝበት፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ ብቻ እየሰማን ከሌላው ጊዜ በተለይ ለእርሱ የምንገዛበት ነው ሲሉም ቃለ ቡራኬያቸውን አሰምተዋል።

ጾሙ ለእምነቱ ተከታዮች የመንፈስ መሳሪያዎች በሆኑት በፍቅር፣ በደስታ፣ በሰላም፣ በትዕግስት፣ በቸርነት፣ በእምነት፣ በበጎነት እና ራስን በመግዛት መጥፎ ተግባራትን ለማሸነፍ የሚቻልበት መሆኑንም ገልፀዋል።

በመጨረሻም ለሚቀጥሉት 55 ቀናት በሚቆየው ጾም ፈቃደ ሥጋን ፣አድመኝነት፣ መለያየት፣ መግደል፣ ምቀኝነት እና ሌሎችንም ክፉ ምግባሮችን በመዋጋት ወደ አንድነት ማምራት የሚቻልበት መሆኑንም አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም