ቀጥታ፡

የአድዋ ጦርነት ላይ የተሳተፈው ሰራዊት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚወክል ህብረ ብሔራዊ ነበር - የታሪክ ምሁራን

አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 በአድዋ በጣሊያን ላይ የተገኘው ድል ሲመዘገብ በጦርነቱ ላይ የተሳተፈው ሰራዊት ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚወክል ህብረ ብሔራዊ እንደነበር የታሪክ ምሁራን ተናገሩ።

''አድዋ የሰውነት ማህተም'' በሚል መሪ ሃሳብ የአድዋን ታሪክ ለመዘከር ከየካቲት 16 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የሚካሄደው ክብረ አድዋ አካል የሆነው ጉባኤ ዛሬ በብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተመጻህፍት ኤጀንሲ ተካሂዷል።

በጉባዔው ላይ የታሪክ ምሁራን የአድዋን ታሪክ የተመለከተ የመወያያ ጽሁፍ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ዳይሬክተር ዶክተር አህመድ ሐሰን ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍ የኢትዮጵያ ህዝቦች ባላቸው ታሪካዊ አንድነት የጣሊያንን የቅኝ አገዛዝ ወረራን ተዋግተው ለድል በቅተዋል።

ከጣሊያን ጋር ወደ ጦርነት መግባቱ አይቀሬ መሆኑ ከታወቀበት ጊዜ ጀምሮ በአራቱም ማዕዘን ዝግጅት በማድረግ ሁሉም በጦርነቱ መሳተፉን ጠቅሰዋል።

ንጉሰ ነገስት አጼ ምኒሊክ ወራሪውን የጣሊያን ጦር እየተስፋፋ መሆኑን በመግለጽ ለህዝቡ ባቀረቡት የክተት አዋጅ መሰረት ወደ ጦር ግንባር የተመመው ሃይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሆኑን የገለጹት ዶክተር አህመድ ''በጦርነቱ ተሳትፎ ድል ያስመዘገበው ሰራዊት ህብረ ብሔራዊ ነበር'' ብለዋል።

ኢትዮጵያውያኑ 'የአድዋ ጦርነት ለኔ ምኔ ነው' ሳይሉ በአንድነት አገር የመከላከል ሃላፊነታቸውን በመወጣት ለድል መብቃታቸውን ተናግረዋል።

ከጣሊያን ጋር የተደረገው ጦርነት ዘመቻ ከጅምሩ እስከ ፍጻሜው ድረስ በጋራ ምክክርና ትብብር መሆኑን አብራርተው ይህ ባይሆን ኖሮ ድሉን ማስመዝገብ እንደማይቻል ገልጸዋል።

''ትውልዱ በጦርና በጎራዴ ብቻ ሳይሆን በጠንካራ የአንድነት መንፈስ ተዋግቶ የድል ባለቤት በመሆን ከቅኝ ተገዢነት ነጻ ያደረገን በመሆኑ ሊመሰገን ይገባል'' ብለዋል።

የኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አልማው ተክሌ 'አድዋና ኢትዮጵያዊነት' በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመወያያ ጽሁፍም ክስተቱ ኢትዮጵያዊነትን ያጠናከረ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

የአድዋ ድል በኢትዮጵያ ታሪካዊ ሆኖ የሚከበረው ጥቁር ህዝቦች በነጮች ላይ ያስመዘገቡት የመጀመሪያ ድል በመሆኑ፣ ዘላቂነት ያለው ተጽዕኖ የሚያሳድር በመሆኑና የአመለካከት ፋይዳ ያለው በመሆኑ እንደሆነ አብራርተዋል።

አድዋ ላይ የተፈጠረው ታሪካዊ ክስተት ነጮች በጥቁር ህዝቦች ላይ የነበራቸውን አመለካከት፣ ግንኙነትና ፖሊሲ እንዲከልሱ ያስገደደ እንደሆነም ገልጸዋል።

በቅኝ ግዛትና በባርነት ስር ይጨቆኑ የነበሩ ጥቁር ህዝቦች ተስፋ የተመለከቱበት ታሪካዊ አጋጣሚ ስለመሆኑም አውስተዋል።

ሁሉም ኢትዮጵያዊ በተሳተፈበት ጦርነት የተገኘው ድል ኢትዮጵያውያንን ያስከበረ በመሆኑ የአሁኑ ትውልድ ከቀደምት አባቶቹ አንድነትን፣ ነጻነት፣ ፍቅርን፣ ህብረ ብሔራዊነትን እንዲሁም ከግል ጥቅም ይልቅ አገርን ማስቀደምን ሊማር ይገባል ብለዋል።

''በአገር ላይ ማመፅና አገርን መበደል የዚያን ትውልድ አደራ መብላት ነው'' ያሉት ዶክተር አልማው አሁን ያለው ትውልድ ከተጣላ፣ ከተከፋፈለ፣ እኔ ብቻ ካለና ስግብግብነት ውስጥ ከገባ የትውልዱን አደራ ለመክፈል እንደማይችልም አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም