በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሦስት ታዋቂ ግለሰቦች መታሰቢያ ኃውልት ሊቆም ነው

258

ሶዶ የካቲት 21/2011 በወላይታ ሶዶ ከተማ ለሦስት ታዋቂ ግለሰቦች የመታሰቢያ ኃውልት ለማቆም የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ፡፡

ኃውልቶቹ  ከቱሪስት መዳረሻነት ባለፈ ታሪክን ለትውልድ ጠብቆ ለማቆየት እንደሚረዱ ተገልጿል።

የወላይታ ዞን ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ መሰረት ድንጋዩን ባስቀመጡበት ወቅት እንደገለጹት ለትውልድ አርአያ ለሆኑ የብሔሩ መሪዎች በስማቸው ኃውልት ማቆም አስፈልጓል።

ምሁራንን ያሳተፈ ኮሚቴ ተዋቅሮ በተካሄደ ጥናት መሰረት ኃውልቶቹ እንዲቆሙ መወሰኑን ተናግረዋል።

"የሚቆሙት ኃውልቶች የጥንትና ዘመናዊ ታሪኮችን የሚያወሱ ናቸው" ያሉት ተጠባባቂ ዋና አስተዳዳሪው ለካዎ ሞቶሎሚ፣ ለካዎ ጦናና  ለቀድሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ  የአቶ ፍሬው አልታዬ ኃውልቶቹ የሚቆሙ መሆናቸውን አመላክተዋል።

የኃውልቶቹ ዲዛይን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን መከናወኑን ገልጸው ኃውልቶቹን የማቆም ሥራ በቅርቡ እንደሚጀመር ተናግረዋል።

በምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ማዕረግ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ጌታሁን ጋረደው በበኩላቸው የቀድሞ አባቶች የህዝቡን ማንነት ለማቆየት ያካሄዱትን ትግልና ገድል ማሳየት በራሱ ታርክ የሚሰራ ትውልድ ለመፍጠር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

"ኃውልቶቹን ለማቆም ያስፈለገው የወላይታን ህዝብና የብሔሩን ታሪክ ትውልድ ተሻጋሪ በማድረግ በህዝቡ ውስጥ አንድነትን ለማጠናከር ነው" ብለዋል፡፡

በዞኑ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት መምሪያ የባህል ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አዳነ አይዛ አካባቢውን ካስተዳደሩ ከ50 በላይ ታዋቂ ግለሰቦች ሦስቱ በግለ-ታሪካቸው መነሻ መሰረት መመረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

ካዎ ሞቶሎሚ10ኛው የወላይታ ንጉስ ሲሆኑ ከ1251 እስከ 1298 ዓ.ም ድረስ አካባቢውን አስተዳድረዋል።

ካዎ ጦና ጋጋ ከ1866 እስከ 1887 ዓ.ም ያስተዳደሩ ሲሆን  ከዘመኑ መሪዎች ደግሞ አቶ ፍሬው አልታዬ መመረጣቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም