የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች ጋር ተወያዩ - ኢዜአ አማርኛ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች ጋር ተወያዩ
አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ዲፕሎማቶች እና ሰራተኞች ጋር መወያየታቸውን የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ ጽህፈት ገለጸ።
ፅህፈት ቤቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው ሚኒስትሩ በጅቡቲ በእድሳት ላይ የሚገኘውን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከጎበኙ በኋላ ከኢምባሲው ሰራተኞች ጋር በአጠቃላይ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱም ሚኒስትሩ በቀጣይ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ዙሪያ አቅጣጫና መመሪያ መስጠታቸው ታውቋል።
ዶክተር ወርቅነህ በ46ኛው የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ ለመሳተፍ ከሁለት ቀናት በፊት ወደ ጅቡቲ ማቅናታቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር እንደመሆኗ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በሰብሳቢነት መርተዋል።
የኢጋድ አባል አገሮች የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ተወካዮች በተገኙበት የተካሄደው ስብሰባ የተለያዩ ውሳኔዎች ተላልፈውበታል።
የኢጋድን አሰራር ለማዘመን በቀረበው ማሻሻያ ላይ ውይይት በማድረግ የቀረበው የማሻሻያ ሃሳብ እስከ ቀጣዩ የሚኒስትሮች መደበኛ ስብሰባ በሚመለከተው አካል በኩል ተጨማሪ ውይይት ተደርጎበት ለቀጣይ ውሳኔ እንዲቀርብም ተወስኗል።
ጉባዔው በቀይ ባህርና በባህረ ሰላጤው አካባቢ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት የሚያስችል ቀጠናዊ አሰራር ከአፍሪካ ህብረትና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር መፍጠር በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በመምከር ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል።