አምባሳደር ፍጹም አረጋ የጉዲፈቻ ልጃቸውን ተረከቡ - ኢዜአ አማርኛ
አምባሳደር ፍጹም አረጋ የጉዲፈቻ ልጃቸውን ተረከቡ
አዲስ አበባ የካቲት 21/2011 በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ የጉዲፈቻ ልጃቸውን ከክበበ ፀሃይ ህጻናት ማሳደጊያ ተረከቡ።
የአዲስ አበባ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ "ጀግኒት ጀግኖችን ትቀርጻለች" በሚል መሪ ሀሳብ ከፌደራል እስከ ወረዳ ያሉ ከፍተኛ ሴት አመራሮች በሰላም ዙሪያ የልምድ ልውውጥ ውይይት አድርገዋል።
በዚሁ የውይይት መድረክ ላይአምባሳደር ፍጹም አረጋ የሶስት ሳምንት እድሜ ያላትን ህጻን ልጅ ለማሳደግ ተረክበዋል።
አምባሳደሩ ህፃኗን ለማሳደግ የወሰኑት ከባለቤታቸው እና ከሶስት ወንድ ልጆቻቸው ጋር ተመካክረው በመስማማታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።
"ህፃኗን ስላገኘን እኔና ቤተሰቦቼ ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል" ያሉት አምባሳደሩ ሌሎችም አቅም ያላቸው ዜጎች ልጆችን በጉዲፈቻ ወስደው እንዲያሳድጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ እና የክበበ ጸሃይ ህጻናት ማሳደጊያም ለአምባሳደር ፍጹም ምስጋና አቅርበዋል።
የአዲስ አበባ የሴቶች እና ህጻናት ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ አልማዝ አብርሃ አምባሳደር ፍጹም ያደረጉትን ተግባር ሌሎችም ሊጋሩት የሚገባ መልካም አርአያ መሆኑን ተናግረዋል።