ቀጥታ፡

የፌዴራሉ ስርዓት ያስገኛቸው ድሎች እንዲጠበቁ የወጣቱ አዲስ አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚገባ ተመለከተ

አክሱም ግንቦት 21/2010 ሀገሪቱ በምትከተለው የፌደራልዝም ስርዓት የተገኙ ድሎች እንዲጠበቁ  የወጣቱ አዲስ አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚገባ ተመለከተ፡፡ የአክሱም ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ 27ኛው የግንቦት 20 በዓል በፓናል ውይይት ሲከበር ባለፉት ዓመታት በሀገሪቱ የተመዘገቡ ለውጦችና እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ላይ የመነሻ ጽሑፎች ቀርበዋል። ጽሁፍ ካቀረቡት መካከል የህወሓት/ኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባል አቶ ጌታቸው ረዳ እንዳመለከተት ባለፉት 27 ዓመታት በግብርና፣በመሰረተ ልማትና በሌሎችም ዘርፎች የተመዘገቡ ታላላቅ ድሎችና ለውጦች የግንቦት ሃያ ድል ቱርፋቶች ናቸው፡፡ ለኢትዮጵያ ደህንነት፣ ሰላምና እድገት ዋስትናው የፌዴራሊዝም ስርዓቱና ህገ መንግስቱ መሆኑን ጠቁመው በዚህ ስርዓት የህዝቦችን ሁለንተናዊ ተሳትፎ እውን ማድረግ እንደሚቻል ገልጸዋል። "በተገኙ ሀገራዊ ስኬቶች ላይ በማትኮር የፌዴራሊዝም ስርዓት ለማጎልበት መላው የሃገሪቱ ህዝቦች መረባረብ አለባቸው" ብለዋል። የተመዘገቡ ለውጦች በማስቀጠል አሁን መንግስት በጀመረው ማስተካከያ ሀገራዊ አንድነትና የፌዴራሊዝም ስርዓቱ ይበልጥ ማጠናከር እንዳሚቻል ነው አቶ ጌታቸው በጹሁፋቸው ያመለከተት። "እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታትና የሀገሪቱን ዘላቂ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በጽኑ መሰረት ላይ ለማረጋገጥ መንግስት ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ይገኛል "ብለዋል። ድህነትን ለማሸነፍ በተደረገው ትግል የተገኘውን ለውጥ  ለማስቀጠል ሁሉም ዜጋ በአንድነት መስራት እንዳለበት ጠቁመው "ክራይ ሰብሳቢነት መግታት የሚቻለው ተስፋ፣ልማት፣እኩልነትና ፍትሕ ሲኖር ብቻ ነው" ሲሉ አቶ ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ስለመብቱ የሚያውቀውን ያህል ስለ ግዴታው የሚያውቅ የተሻለ ትውልድ መፍጠር እንደሚያስፈልግ ጠቅሰው በፌደራል ስርዓቱ ምክንያት የተገኙ ድሎችን ከዳር ለማድረስ የወጣቱን አዲስ አስተሳሰብ በተለየ ሁኔታ ማስተናገድ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡ ሀገሩን ለመለወጥ የሚጥር የተማረ የሰው ኃይል በማፈራት በኩል ምሁራን መስራት እንዳለባቸውም ጠቁመዋል። የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጸሐዬ አስመላሽ በበኩላቸው፣ ህገ መንግስቱና የፌደራል ስርዓቱን ለማጎልበት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በጥናትና ምርምር  ስራ ማገዝ እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል። ስርዓቱን ለማስቀጠልና የጋራ አስተሳሰብ ለማዳበር ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል። የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ለሀገራዊ አንድነት ፈተና የሆነውን ብሄርተኝነት ለመከላከል ክልሎች ከራስ አስተዳደር ባለፈ ለፌዴራል አስተዳደሩም ትኩረት መስጠት እንዳለባቸው ጠቁመዋል። በየተሰለፉበት መስክ ሀገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት እንደሚያገለግሉም ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም