ቀጥታ፡

በነገሌና አዶላ ወዩ ከተሞች በ274 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወሰደ

ነገሌ ካቲት 20/2011 በህገወጥ መንገድ ሲንቀሳቀሱ የተገኙ 274 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መውሰዱን የጉጂ ዞን ገቢዎች ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በዞኑ ነገሌና አዶላ ወዩ ከተሞች በግማሽ የበጀት ዓመቱ በተደረገ ቁጥጥርና ክትትል ድርጅቶቹ  ላይ እርመጃ መወሰዱ ተገልጿል ።

በጽህፈት ቤቱ የህግ ማስከበር ባለሙያ አቶ ሀብታሙ ገብረሀና ለኢዜአ እንዳሉት  እርምጃ ከተወሰደባቸው ድርጅቶች ውስጥ 129ኙ  ለተጠቃሚ ደረሰኝ ባለመስጠት የተገኙ ናቸው።

ሌሎች 145ቱ ገቢና ወጪያቸው እንዳይታወቅ ያለመመዝገቢያ ማሽን ሲሰሩ የተደረሰባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ጽህፈት ቤቱ  ከእነዚህ የንግድ ድርጅቶች መካከል 58 የቃልና 113   የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል።

ቀሪዎቹ ደግሞ  ሶስት ሚሊዮን 700 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ገልጸዋል

"በክትትልና ቁጥጥሩ 422 ነጋዴዎችም  ተመዝግበው ወደ ህጋዊ ግብር ከፋይነት እንዲገቡ ተደርጓል" ብለዋል ።

ግብር ለመሰወር በሚሞክሩና በህገ ወጥ መንገድ የሚሰሩ ነጋዴዎችን ፈቃድ ከመቀማት እስከ እስራት የሚያደርስ አሰራር መዘርጋቱን ባለሙያው ተናግረዋል።

በጽህፈት ቤቱ የእቅድና በጀት ክትትል ባለሙያ አቶ ንጉሴ ዱጎ በበኩላቸው በግማሽ የበጀት ዓመቱ ከ179  ሚሊዮን ብር  በላይ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

ገቢው የተሰበሰበው ከ14 ወረዳዎችና ሶስት የከተማ አስተዳደሮች መሆኑን አመልክተው "ገቢው ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ከእቅዱ ደግሞ በ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ብልጫ አለው" ብለዋል ።

በነገሌ ከተማ በሆቴል ንግድ ስራ የተሰማሩት አቶ መለሰ ሽፈራው "ግብር መክፈል ውዴታ ብቻ ሳይሆን ሀገራዊ ግዴታም መሆኑን እገነዘባለሁ " ብለዋል።

በህጋዊና ህገ ወጥ መንገድ  የሚሰሩ ነጋዎችን መለየት ተገቢ  መሆኑን ገልጸው  ደረሰኝ የማይቆርጡ፣  ወጪና ገቢ የማያሳውቁ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ እንደሚደግፉ  ተናግረዋል ።

በህገ ወጥ አሰራር ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር የአንድ ወቅት ብቻ መሆን እንደሌለበት የተናገሩት ደግሞ  በሸቀጣ ሸቀጥ ንግድ የተሰማሩት  አቶ ሁሴን ሙስጠፋ ናቸው።

"አንዱ ግብር ከፍሎ ህጋዊ ሆኖ ሲሰራ ሌላው እያምታታ የንግድ ስራውን የሚያዛባ ከሆነ ሀገርና መንግስትን ብቻ ሳይሆን ተጠቃሚውንም ህዝብ የሚጎዳ ነው" ብለዋል፡፡

በጉጂ ዞን  በበጀት ዓመቱ ከ11 ሺህ 400 መደበኛ ግብር ከፋዮች 334  ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም