አድዋ - የጥቁሮች ህዝቦች የነጻነት እርሾ

ሰለሞን ተሰራ (ኢዜአ)

በጀርመን በርሊን ከተማ የሚገኘው ውብ የሆነው የቻንስለር ቬን ቢስማርክ መኖርያ ሳሎን ፌሽታ በፌሽታ ሆኗል። እለቱ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር የካቲት 16 ቀን 1885 ሶስት ወር ሙሉ አሰልቺ ውይይት የተደረገበትና ዋና ዋናዎቹ የአውሮፓ ቅኝ ገዢዎች ተሰብስበው ''አንተ ይሄን ያዝ አንተ ያንን ያዝ'' ተባብለው ከወታደራዊ ዘመቻ በፊት አፍሪካን የተቃረጡት።

በስብሰባው ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን የአፍሪካ መሬት የሃሳብ መስመር እያሰመሩ ያለከልካይ ተከፋፈሉት። የበርሊኑ ''General act of Berlin conference'' በታሪክ አፍሪካን የመቀራመት ጉባዔ (''The division of Africa/scramble of Africa'') ተብሎ ይታወቃል። በጉባኤው ላይ የጀርመን፣ ኦስትሮ-ሀንጋሪ፣ ቤልጅየም፣ ዴንማርክ፣ ፈረንሳይ፣ ብሪታንያ፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስና ፖርቱጋል ተወካዮች ተገኝተዋል።

አውሮፓውያን አፍሪካን ለመቀራመት በበርሊን ስምምነት ሲያደርጉ፤ አፍሪካዊያን ደግሞ የውጭ ወራሪዎችን ለመከላከል ከዚህ አለፍ ሲልም  እርስ-በርሳቸው መተነኳኮስ የጀመሩበት ጊዜ እንደነበር ነበር። ወቅቱ በአራቱም የአህጉሪቷ አቅጣጫ የሚገኙ ንጉሶችና የጭፍራ አለቆች በተናጠል ከአውሮፓውያኑ ጋር በገጠሟቸው ውጊያዎች ትርጉም ያለው ስኬት ሳያገኙ፤ አፍሪካውያን በቅኝ ግዛት መውደቅ የጀመሩበት ነው።

ይህን ተከትሎ ጣሊያንም ኢትዮጵያን በቁጥጥሯ ስር ለማድረግ ብትነሳም እምቢተኛው ጥቁር ህዝብ ማንነቱንና ክብሩን አሳልፎ ላለመስጠት በመወሰኑ ያልተመጣጠነ ውጊያ ቢገጥሙም አሳፍሮ መልሷታል። ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀው የጣሊያን ጦር  የቅኝ ግዛት ተልእኮውን እውን ለማድረግ የተመመው በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በአግባቡ የሰለጠኑ ወታደሮችን ይዞ ነው። ነገሩ እንደታቀደው ሳይሆን ቀርቶ የጣሊያን ጦር በአድዋ ድል ተነሳ።

የታሪክ ሊቃውንት እንደሚያስቀምጡት፤ የአድዋ ጦርነት በአፍሪካ ምድርና ታሪክ ከተከናወኑት ጦርነቶች ከፍተኛውን የዋጋና የክብር ስፍራ ይዟል። አኒባል የአልፕን ተራሮች ዞሮ የአውሮፓን ኃያል መንግሥት ካሸነፈ ወዲህ፣ አንድ አውሮፓዊ ጦር በአፍሪካውያን ጦር ሲሸነፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ነበር። ስለሆነም፣ ጦርነቱ ብዙ መልክና ብዙ ቅጽል ተሰጥቶታል።

የአድዋ ድል ለኢትዮጵያ ነጻነትና ኩራትን፤ በአለም ዙሪያ በተለይ በአሜሪካዎቹ ሰፋፊ እርሻዎች ለ500 አመታት በባርነት ለተጋዙ ጥቁር ህዝቦች ደግሞ፤ የማንነት ማረጋገጫ፣ የዘመናት ጭቆናና የስነ-ልቦና ቁስልን አውልቆ የመጣያ የተስፋ ትንሳኤ ሆኖም ነበር።

ፖል ሄንዝ በጻፉት የታሪክ ድርሳን "አውሮፓውያን የፈለጉትን ገድለዋል፣ ባሪያ ፈንግለዋል፣ አካባቢን፣ ሀብትን፣ ጉልበትን መዝብረዋል፣ ምክንያቱ በግልጽ ባይታወቅም 'ኢትዮጵያን በጦር ከማስገበር ይልቅ እንቃረጣት ብለው' ብሪታኒያ፣ ፈረንሳይና ጣሊያን የሶስትዮሽ ስምምነት 'Tripartite agreement' ተፈራርመው ምኒልክን 'እወቁልን' ብለው ጦማር ሰደዋል። ምኒልክም 'ስለነገራችሁኝ አመሰግናለሁ፣ ነገር ግን እኔ በሌለሁበት የተወሰነውን አላውቅም' በማለታቸው ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራ ያዘች።

ወረራውን ለመቀልበስ በአጼ ምኒልክ የሚመራው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ትግል ቢያደርግም የወራሪዎቹ ብልጣብልጥነት ጦርነቱን አይቀሬ አደረገው። ወደ ጦርነት ተገዶ የገባው የኢትዮጵያ ሃይል በአምባላጌ፣ በመቀሌና በአድዋ በተከታታይ ባደረገው ጦርነት የበላይነት ወስዶ የካቲት 23 ቀን 1988 ዓ.ም ላይ በአድዋ የድል ባለቤት መሆኑ ተበሰረ። የድሉ ዜና እንደናኘ በአፍሪካ ተስፋ፣ በአውሮፓ ድንጋጤ ፈጠረ። የኢትዮጵያ ድል አውሮፓውያን በአለም የነበራቸውን ልእለ ሀያልነት ለመጀመሪያው ጊዜ ጥያቄ ውስጥ ከቷል። ፖል ሄንዝ ''ዛሬ ላይ ሆነን ስናየው" የኢትዮጵያ ድል የአውሮፓ ተሰሚነት የቁልቁለት ጉዞ መነሻ ነበር።" ሲሉ በጽሁፍ አስፍረዋል።

ድሉ እንግሊዝ ኢትዮጵያን በእኩል አይን አይታ ''የምስራቁን የደቡቡን የምእራቡን ድንበራችንን እንካለል'' ብላ በፊርማ እንድታጸድቅ አስገድዷታል። ከዚህ በተጨማሪ በአውሮፓ ቅኝ ግዛት መዳፍ ስር ሲማቅቁ የነበሩትን አፍሪካውያን እና ካሪቢያን ጥቁሮች ለነፃነታቸው እንዲታገሉ ብርታት እና ምሳሌ ሆኗቸዋል። ለጥቁር አሜሪካውያን ምሁራን ከፍተኛ የመንፈስ መነቃቃት እንዲያገኙ አድርጓል።

የአድዋ ድል ቁጭት ፈጥሮ ከ30 አመት በኋላ ፋሺዝም በጣሊያን ውስጥ ስር እንዲሰድ እና መሪ የፖለቲካ አይዲዮሎጂ እንዲሆን ምክንያት ሆኗል። ለኢትዮጵያ ደግሞ የተረጋጋ መንግስታዊ አስተዳደር አስገኝቷል። በዚህ የከሸፈ የቅኝ-ግዛት እቅድና የአውሮፓውያን ተስፋፊነት የተደሰቱ ሶሻሊስት አመለካከት ያላቸው ወገኖች በጣሊያን፣ በእንግሊዝና በፈረንሣይም ነበሩ።

ሪቻርድ ፓንክረስት THE BATTLE OF ADWA የተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ እንዳሰፈሩት የኢጣሊያኑ ክሪቲካ ሶሻሌ (Critica Sociale) ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ቱራቲ በወኔና በምልዓት ለእውነት ስለእውነት ጻፈ። “ጣሊያን ወደ ዐድዋና ወደ ሌሎችም ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ተደረጉት ጦርነቶች የገባችው፣ ለእንግሊዛውያን አገልጋይና አሽከር ሆና ነው። በዚህም የተነሳ የጣሊያናውያን ሀብትና ደም ያላግባብ ፈሰሰ።” ሲል ወረራውን በማውገዝ ድፍረት የተሞላበት ጽሁፉን ማስነበቡን ይገልጻሉ።

ጋዜጠኛው በጽሁፉ “የጣሊያንና የእንግሊዝ መንግሥታት በአፍሪካ ስለተቀዳጁት የቅኝ-ግዛትና የተስፋፊነት ድል እንደጽጌረዳ የፈካ ውሸት እየፈበረኩ ይመጻደቁ እንጂ፣ በእርግጥ ኢትዮጵያ ድል አድርጋለች። ...ቪቫ ምኒልክ! ቪቫ ኢትዮጵያ!” ሲል አወድሷል።

በአጼ ምኒልክ መሪነት የኢትዮጵያ ሃይል በጣሊያን ወራሪ ሃይል ላይ በአድዋ የተቀዳጀው ድል ድልድይ ሆኖ የጥንታዊቷን ኢትዮጵያ የታላቅነት ክብር ከዘመናዊ ዓለም ጋር ያገናኘ ድልድይ ሆኗል። ታዲያ ይህ ድልድይ በ1890 ዎቹ ግንባታው የተጀመረው የተቀረው የአፍሪካ ክፍል በውጭ ሃይሎች አገዛዝ ቀንበር ስር ሲወድቅ ኢትዮጵያውያን ብቻ በተከታታይ የተሰነዘረባቸውን ወረራ በድል ሲመልሱ ነበር።

በዚያው ክፍለ ዘመን ኢትዮጵያውያን ለውጭ ወራሪዎች የማይንበረከኩ መሆናቸውን ማሳየታቸውን ማስታወስ ይቻላል። በ1870 ዎቹ የግብፃውያንን፣ በ1880 ዎቹ የመሃዲስቶችን ተደጋጋሚ ጥቃቶች መክተው መልሰዋል። የአድዋ ድል ደግሞ ይህን የነፃነት ቀናዒነት ይበልጥ ከማድመቅ አልፎ የዓለምን ትኩረት ስቧል።

የአውሮፓ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውን ወደ አዲስ አበባ እንዲልኩ፣ ከኢትዮጵያ ጋር 19 ድንበርን የሚመለከቱ ስምምነቶችን እንዲፈራረሙ አደረጋቸው ። በአርነት ትግሉ መስክ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩት እህት የአፍሪካ አገሮች ታጋዮችም ኢትዮጵያ ፋና ወጊ መብራታቸውና የራዕይ ምንጫቸው ነበረች።

የዓድዋ ድል የፓን አፍሪካን ንቅናቄ መሰረት መሆኑን የኢትዮጵያውያንን የአድዋ ውሎ ከዘከሩ የታሪክ ጠበብት መካከል የዋሽንግተኑ የታሪክ ሊቅ ፕሮፌሰር ራየሞንድ ጆናስ “The Battle of Adwa-African Victory in the Age of Empire'' በሚለው ጽሁፋቸው አስፍረዋል፡፡ በዚህ ጽሁፋቸው “የአድዋ ድል ለአፍሪካውያን ቅኝ አገዛዝን ታግሎ መጣል እንደሚቻል ያሳየ፤ የኢትዮጵያንም ታላቅነት ያስመሰከረ” ስለመሆኑ ደጋግመው አውስተዋል።

ለዚህም ነው የናይጄሪያ ድኀረ ነፃነት የመጀመሪያ ፕሬዚዳንት የነበሩት ዶክተር ናምዲ አዚኪዊ “ኢትዮጵያ ጥቁር ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርባት አገር ነች። በዚህ ክፍለ አህጉር ላይ የአፍሪካ ቀደምት አባቶች የመሰረቱት መንግሥት የታሪክ ዋቢ ነች። ኢትዮጵያ ከዘመን ወደ ዘመን እየተሸጋገረች ህልውናዋን ጠብቃ መኖሯ የሚደነቅና መደነቅም ያለበት ነው። ” በማለት የተናገሩት።

ከአድዋው ድል አርባ ዓመት በኋላ ጣሊያን ቂሟን ልትወጣ  ወረራ ስታካሂድ በግልጽም ይሁን በተዘዋዋሪ የአውሮፓና የአሜሪካ መንግሥታት ከእሷ ጎን ቆመዋል።

በተቃራኒው ድሉ በአፍሪካም ይሁን በተቀረው ዓለም የተቀጣጠለውን የአፍሪካዊነት የትግል ስሜት አነሳስቷል። እልህ አጭሯል። በአጠቃላይ መላው ጥቁር ህዝብ፣ በቁጥር አነስተኛ ቢሆኑም ለፍትህ የታመኑ አውሮፓዊያን ነጮችም ለኢትዮጵያ ያላቸውን ወገናዊነት እንዲያጠናክሩ ጥርጊያውን አመቻችቷል።

የነኝህም ጥረት በውጭ የነበረውን ህዝባዊ ድጋፍ ወደ ኢትዮጵያ ያደላ እንዲሆን አድርጎታል። ባህላዊ እሴቶቻቸውን ያልጣሉ የአፍሪካ ምሁራን ከነበሩባቸው የአህጉሩ ከተሞች፣ ከካርቢያን ደሴቶች፣ ከጥቁር አሜሪካዊያን በኩል ተሰባስበው ወረራው ያጫረባቸውን የመጠቃት ስሜት በይፋ አንጸባርቀዋል።

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለነበሩት የአፍቃሪ ኢትዮጵያዊነት እንቅስቃሴ መሪዎችም የአድዋው ድል የሞራል እርሾ ሆኗቸዋል። ከእንቅስቃሴው ግንባር ቀደም መሪዎች አንዱ ጀምስ ድዋኔ ግብጽና ሱዳን ውስጥ ያሉትን ክርስቲያን አፍሪካዊያን ሁኔታ ትኩረት ሰጥተው መፍትሄ ይፈልጉለት ዘንድ ለምኒልክ ደብዳቤ የፃፉት የአድዋውን ድል ተከትሎ ነበር።

ስለ አድዋ ድል የእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ዊንስተር ቸርችል “የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ. ም. የአድዋ ጦርነት ተካሂዶ፤ ጣሊያን በኢትዮጵያውያን የደረሰባት ሽንፈት ደረሰባት። (ይህም) ሌሎች ሕዝቦችን የሚነካ ሁለት ውጤቶች አስከተለ፤ አንደኛ፥ ሰሜን አፍሪካ ላይ አውሮፓዊ ክብርን ትልቅ ምች መታው። ሁለተኛ፥ በአውሮፓ ፖለቲካ ማንነት ረገድ የኢጣልያ ዋጋ ወደታች ወረደ።” ብለው ጽፈዋል።

ቸርችል ስለ ኢጣልያ ሽንፈትና ውጤቱ ከመጻፍ ይልቅ ስለ ኢትዮጵያ ድልና በአፍሪካና በሌሎቹ ጭቁን አገሮች ዘንድ የኢትዮጵያን ማንነት ሽቅብ መናሩን መግለጽ አልፈለጉም። ይህ ሊሆን የቻለው ምናልባትም አድዋ ላይ የተገኘው ድል ለጥቁር ህዝቦች ከነጻነት ለመውጣት የተስፋ እርሹ በመሆኑ፣ ለአውሮፓውያኑ የቅኝ ግዛቶቻቸውን ሊያጡ የሚችሉበት ጅምር በመሆኑ ሊሆን ይችላል።

የሆነ ሆኖ አድዋ ላይ የተለኮሰው የድል ችቦ በቅኝ ግዛት ስር ለነበሩት የአፍሪካ አገሮች ቀንዲል ሆኗል። ለዚህም ክብር ለመስጠት 17 የአፍሪካ አገሮች የሰንደቅ ዓላማ ቀለማቸውን ከኢትዮጵያ ወስደዋል። አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀይ የሆነው የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ ቀለም ማሊ፣ ጋና፣ ካሜሩን ... አገሮች በተለያየ ቅርጽ የአገራቸው መለያ ሰንደቅ አላማ እንዲሆን አድርገዋል።3

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም