ቀጥታ፡

በወረኢሉ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ለውድመት እየተዳረጉ ነው

አዲስ አበባ  የካቲት 20/2011 በወረኢሉ ከተማ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶች ሙዚየም ተገንብቶላቸው በአግባቡ ባለመያዛቸው ለውድመት እየተዳረጉ መሆኑ ተገለጸ።

ከተማ አስተዳደሩ በበኩሉ ሙዚየም ለመገንባትና ለአጼ ምኒሊክ መታሰቢያ ሃውልት በከተማዋ ለማቆም እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታውቋል።

123ኛውን የአድዋ ድል በማስመልከት በጉብኝት ላይ የሚገኘው የፌዴራልና የክልል የባህልና ቱሪዝም ሃላፊዎች፣ባለሙያዎች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ወረኢሉ የሚገኙ ታሪካዊ ስፍራዎችን ጎብኝተዋል።

በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የሚመራው የአድዋ ዘማቾች ጦር ማዕከል የነበረችው ወረኢሉ የንጉሰ ነገስቱን ቤተመንግስት ጨምሮ ሌሎች በርካታ ታሪካዊ ቅርሶችን ይዛለች።

ይሁን እንጂ ባለፉት ዓመታት የአድዋ ድል ሲዘከር "የአጼ ምኒሊክ ስም እንዳይነሳና የወረኢሉ ታሪካዊ ስፍራነት እንዳይነገር" ሲደረግ መቆየቱን የከተማዋ ከንቲባ አቶ እሸቱ ታረቀኝ ለኢዜአ ገልጸዋል።

የአድዋ ጦርነት የክተት አዋጅ የተጠራባት ወረኢሉ ታሪኳ እንዳይታወቅና ቅርሶቹ ለቱሪስት መዳረሻ እንዳይውሉ አሉታዊ ተጽእኖ ፈጥሯልም ነው ያሉት።

በከተማዋ በጦርነቱ አብሮ የዘመተውን የቅዱስ ጊዮርጊስ ጽላትን የያዘችው የወረኢሉ ደብረሰላም ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተክርስትያን ፣የዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግስትና ልዩ ልዩ ታሪካዊ ቅርሶች ይገኛሉ።

ሆኖም ከደርግ ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ቤተ መንግስቱ እንደ ቅርስ ሳይሆን ለቢሮነት እያገለገለ በመሆኑ ለጉዳት እየተዳረገ መሆኑን አስረድተዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ቅርሶቹን ለመጠበቅና የቱሪስት መስህብ ለማድረግ እንዲሁም የሙዚየም ግንባታ ለማከናወን የገንዘብ ማሰባሰብ ስራ መጀመሩንም ገልጸዋል።

እንደ አቶ እሸቱ ገለፃ በከተማዋ በዳግማዊ አጼ ምኒሊክ ስም ሙዚየም ለመገንባትና ሃውልታቸውንም ለማቆም የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል።

ወረኢሉ ከአድዋ ጋር ካላት ታሪካዊ ግንኙነት አንጻር በአድዋ የሚገነባው የፓን አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ቅርንጫፍ በወረኢሉ እንዲከፈት ጥረት እየተደረገ ነውም ብለዋል።

የወረኢሉ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ሰበካ ጉባኤ አገልጋይ ቀሲስ አንተነህ ልኡልሰገድ እንደሚሉት በ13ኛው ክፍለ ዘመን በአጼ ነዓኩተለአብ የተመሰረተችው ቤተ ክርስትያኗ በርካታ ታሪካዊ ቅርሶች ይዛለች።

እድሜ ጠገብ የብራና መጽሃፍ፣ የዳግማዊ አጼ ምኒሊክ የንግስ አክሊል፣ የእቴጌ ጣይቱና የንግስት ዘውዲቱ የራስ አክሊል፣ በወርቅና በብር የተሰሩ ካባዎች፣ ለምዶች፣ ዣንጥላዎችና ሌሎች ንዋየ ቅዱሳት ይገኛሉ።

ይሁንና ቤተክርስትያኗ የያዘቻቸው ጥንታዊ ቅርሶች ሙዚየም ተገንብቶላቸው በአግባቡ ባለመያዛቸው ለውድመት እየተዳረጉ መሆኑን ቀሲስ አንተነህ ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በተፈጸመ ስርቆት የአድዋ ታሪክ የተጻፈበትን ከበሮ ጨምሮ ሌሎች በርካታ ንዋየ ቅዱሳት መዘረፋቸውንም አስታውሰዋል።

ቤተክርስትያኗ ለቅርሶቹ ሙዚየም ለመገንባት አቅም የላትም ያሉት ሲስ አንተነህ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ድጋፍ እንዲያደርጉና ቅርሶችን ከውድመት እንዲታደጉ ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም