ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በህዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው ተባለ

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፍትሃዊና ውጤታማ የአሰራር ስርዓትን በመዘርጋት በህዝብ ዘንድ ያለውን ተአማኒነት ለማጠናከር እየተሰራ ነው ተባለ።

የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ፌዴሬሽኑ ግልፅ የሆነ የአሰራር እጦትን ጨምሮ በተለያዩ የአሰራር ግድፈቶች የሚታማ ተቋም ሆኖ መቆየቱን አስታወሰዋል።

ባለፈው ዓመት ግንቦት ወር የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ ኃላፊነቱን የተረከበው አካል ይህን ችግር በመፍታት፤ ፌዴሬሽኑን በህዝቡ ዘንድ አመኔታ የሚጣልበትና ፍትሃዊ አሰራር የሰፈነበት ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑ ኮሎኔል አወል ገልጸዋል።

በዚህ ዓመት ግማሽ የውድድር ጊዜ እንቅስቃሴዎች ላይ እንኳ አበረታች የሚባሉ ተግባራት መከናወናቸውን አክለዋል።

ከእነዚህ መካከል የፍትህ አካላት የሆኑት የፌዴሬሽኑ የዲሲፕሊንና ይግባኝ ሰሚ ኮሚቴዎች ከፌዴሬሽኑ ጣልቃ ገብነት ነፃ ሆነው የሚሰሩበትን ሁኔታ አመቻችቷል።

በዳኝነት ላይ የሚነሱትን ቅሬታዎች ለመድፈን አሁንም ብዙ መስራት የሚጠይቅ ቢሆንም ጥሩ ጅምሮች መኖራቸውንም ገልጸዋል።

ባለፈው ዓመት ወደ ኃላፊነት የመጣው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተጫዋቾችን የዝውውር ስርዓት ለማሻሻል የሚያስችሉ እርምጃዎችን ለመውሰድ ማቀዱንም እንደታቀደም ኮሎኔል አወል ገልጸዋል።

አሁን ባለው ሁኔታ ክለቦች የሚያወጡት ወጪና የሚያገኙት ገቢ ተመጣጣኝ ባለመሆኑ በዚህ መልኩ መቀጠል የክለቦቹን የገንዘብ አቅም የሚፈታተን እንደሚሆንም አንስተዋል።

በመሆኑም የተጫዎቾች የዝውውር ጉዳይና የውል ጊዜ በተመለከተ እስከሚቀጥለው ዓመት ድረስ ተጠናክሮ በ2012 ዓ.ም በአዲሱ መመሪያ ለመተገበር እንደታሰበም አስታውቀዋል።

አጠቃላይ እግር ኳሱ የሚታዩ ክፍተቶችን ለመድፈን፣ ውጤታማ የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋትና ተቋሙ ጠንካራ የህዝብ አመኔታ እንዲኖረው ለማድረግ አዲስ አደረጃጀት እየተፈጠረ መሆኑም ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም