ቻይና ለአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረግ ትፈልጋለች ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ለአዲስ አበባ ወንዞች ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት ድጋፍ ማድረግ ትፈልጋለች ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 የቻይና መንግስት በአዲስ አበባ የሚገኙ ሁለት ታላላቅ የወንዞች ዳርቻ ወደ ጽዱና አረንጓዴነት የሚቀይረውን ፕሮጀክት በገንዘብና በቴክኒክ የመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገለፀ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሃሳብ አፍላቂነት በከተማ አስተዳደሩ ሊተገበር የታቀደው አዲስ አበባን የማስዋብ ፕሮጀክት ቻይና የመደገፍ ፍላጎት እንዳላት የመስኩ ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ በመላክ አረጋግጣለች።
የቻይና መንግስት የባለሞያ ልዑካን ቡድን የተጀመረውን ፕሮጀክት በገንዘብ እና በቴክኒክ እገዛ ማድረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ዛሬ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ ጋር ተወያይቷል።
በዚህ ወቅትም የቴክኒክ ቡድኑ የቻይና መንግስት ፕሮጀክቱን የሚደግፍበት ሁኔታ ላይ ጥናት የሚያደርግ ከከንቲባ ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል።
ቡድኑ በመጪዎቹ 7 ቀናት ውስጥ ጥናቱን አጠናቆ ዝርዝር ጉዳዩ ለህዝብ እንደሚገለጽም የከንቲባ ጽህፈት ቤት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጿል።
56 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚኖረው ይህ ፕሮጀክት በአጠቃላይ ወደ 29 ቢሊዮን ብር ወጪ ይደረግበታል ተብሎ ተገምቷል።
በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ፕሮጀክት ለበርካታ የከተማዋ ነዋሪዎች የስራ እድል እንደሚፈጥርም ይታመናል።