ቀጥታ፡

የድሉን የአንድነት እሴት በተግባር በማሳየት አድዋን ማክበር እንደሚገባ ተገለጸ

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 ''ኢትዮጵያዊያን አድዋን ስንዘክር የድሉን የአንድነት እሴት በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል'' ሲሉ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ተናገሩ።

የኢትዮጵያዊያንን የጋራ ታሪክ በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ ለማካተት ዝግጅት መደረጉንም ገልጸዋል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መንፈስ ሉዓላዊነታቸውን አስከብረው ለትውልድ ማስተላለፋቸውን ነው የገለጹት።

ይህን የኢትዮጵያዊያን፤ ብሎም የጥቁር ህዝቦች አኩሪ ታሪክ አስጠብቆ ማቆየትና እሴቱን መከተል የወጣቱ ኃላፊነት መሆኑንም ነው የገለጹት።

''ኢትዮጵያዊያን አድዋን ስንዘክር የድሉን የአንድነት እሴት በተግባር በማሳየት ሊሆን ይገባል'' ያሉት ሚኒስትሯ የዘንድሮው በዓል ትኩረቱን አንድነትን ማጉላት ላይ ማድረጉን ይገልጻሉ።

የኢትዮጵያዊያንን የጋራ ታሪክ በስርዓተ-ትምህርት ውስጥ በማካተት ከትውልድ ትውልድ ታሪክ ሳይዛባ እንዲተላለፍ ለማድረግ ዝግጅት መደረጉንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል።

ትክክለኛውን የኢትዮጵያ የጋራ ታሪክ በመማሪያ መጽሃፍት ለማካተት የታሪክ ምሁራን ኃላፊነት የጎላ ነው ብለዋል ሚኒስትሯ።

ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የኢትዮጵያዊያን የጋራ ታሪክ በስርዓተ-ትምህርት እንዲካተት ሰነድ አዘጋጅቶ ለትምህርት ሚኒስቴር መስጠቱን ተናግረዋል።

እንደ ዶክተር ሂሩት ገለጻ፤ የአድዋን ድል በዓል ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ጎብኚዎች መስህብ ለማድረግ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ ነው።

ከዚህም ውስጥ ከአንጎላላ አስከ አድዋ የቱሪስት መስመር በመክፈት ጎብኚዎች ሙሉ ለሙሉ የአድዋን ታሪክ እንዲረዱ ማድረግ አንዱ ነው።

ይህም የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲጨምር ከማድረግ ባለፈ ታሪክን በትክክል ለትውልድ ለማስተላለፍ ይረዳል ብለዋል።

የቱሪስት መስመሩ ዓመቱን ሙሉ ለአገር ውስጥና ለውጭ አገር ዜጎች ክፍት የሚሆን ነው።

የአድዋን ድል የአፍሪካዊያን የነጻነት ታሪክ መሆኑን የሌላ አገር ዜጎች በአግባቡ ከማወቅ ባለፈ በመጽሃፍ ጽፈው ማስቀረታቸውን የገለጹት ዶክተር ሂሩት ''እኛ ኢትዮጵያዊያን ይህን ታሪክ በአግባቡ ማወቅና እሴቱ እንዲቀጥል የማድረግ ኃላፊነት አለብን'' ብለዋል።

123ኛው የአድዋ ድል በዓል ''አድዋ የኢትዮጵያዊያን የአንድነታችን ማህተም ''በሚል መሪ-ሀሳብ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም