የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተርጓሚዎች አለመገኘት ሳቢያ የተከሳሾችን የክስ መዝገብ መስማት ሳይችል ቀረ - ኢዜአ አማርኛ
የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በተርጓሚዎች አለመገኘት ሳቢያ የተከሳሾችን የክስ መዝገብ መስማት ሳይችል ቀረ
አዲሰ አበባ የካቲት 20/2011 የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በቀድሞ የሱማል ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አብዲ መሐመድ ኡመር መዝገብ የተከሰሱትን አቶ ዋርሰሜ ሽህ አብዲ እና አቶ ጉሌድ አበል ክስ መስማት ሳይችል ቀረ።
ግለሰቦቹ ክስ የቀረበባቸው ባለፈው ዓመት ከኃምሌ መጨረሻ ላይ በሱማሌ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ግድያንና መፈናቀልን ጨምሮ ከተፈፀመ ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት ተግባራት ጋር በተያያዘ ነው።
ፍርድ ቤቱ ለዛሬ የቀጠረው የሚቀርብለትን የግለሰቦቹን ክሰ በንባብ ለማድመጥ ነበር።
ሆኖም ተከሳሾቹ አማርኛ ቋንቋ የማይችሉ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬሽን የሶማልኛ ቋንቋ ክፍል ተርጓሚዎች እንዲመጡ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ቢሰጥም ተርጓሚዎቹ በዛሬው እለት አልተገኙም።
በዚህም የተነሳ ተከሳሾቹ ተጠያቂ የሚሆኑበትን ክስ ለማሰማት ሳይቻል ቀርቷል።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንክ ኮርፖሬሽን የሶማልኛ ቋንቋ ክፍል ተርጓሚዎች በመጪው መጋቢት 20 ቀን 2011 ቀርበው የማስተርጎም ተግባሩን እንዲከውኑ፤ በዛሬው እለትም ያልቀረቡበትን ምክንያት እንዲያስረዱ ትእዛዘ ሰጥቷል።
በዚሁ መዝገብ ክስ የቀረበባቸው 47 ሰዎች ሲሆኑ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋሉት ግን 6 ብቻ ናቸዉ።
ፍርድ ቤቱም ፖሊስ እነዚህን ተከሳሾች በቁጥጥር ስር አውሎ እንዲያቀርብ ትእዛዝ ሰጥቶ የነበረ ቢሆንም በአድራሻቸው ሊያገኛቸው አለመቻሉን ፖሊስ ጸናግሯል።
በመሆኑም ማስረጃ ለማምጣት ተለዋጭ ቀጥሮ እንዲሰጠውም ጠይቋል።
ፍርድ ቤቱም ለዚህም ጉዳይ ለመጋቢት 20 ቀን ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል።