ቀጥታ፡

በትግራይ ከተሞች ቤት ለሌላቸው ቦታ ለመስጠት ምዝገባ እየተካሄደ ነው

መቀሌ የካቲት  20/2011 በትግራይ ክልል ከተሞች የመኖሪያ ቤት ችግር ላለባቸው ሰዎች ቦታ ለመስጠት ምዝገባ እየተካሄደ መሆኑን  የክልሉ ፍትህ ቢሮ አስታወቀ፡፡

ከየካቲት 18/2011ዓ.ም  ጀምሮ እየተካሄደ ያለው ምዝገባ በክልሉ 12 ከተሞች ቤት ለመስራት አቅም ያላቸውን ነዋሪዎች በማህበር በማደራጀት ጭምር ነው፡፡

ይህም ተግባር ምዝገባው የክልሉ ስራ አስፈፃሚ ምክር ቤት የመኖሪያ እጥረትን ለማቃለል ጥር 23 ቀን 2011 ዓ.ም. ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት  መሆኑን በቢሮው የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ የስራሂደት ዳይሬክተር ወይዘሮ ርግበዳዊት አርአያ ለኢዜአ ተናግረዋል፡፡

"ነዋሪዎች ቦታውን ለማግኘት 20 ሆነው በመደራጀት 48ሺህ ብር መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል ።

ነዋሪዎች ቁጠባቸውን እስኪያጠናቅቁ በከተሞች ቦታ የመለየትና የካሳ ክፍያ የመፈፀም ስራ እንደሚከናወን አመላክተዋል ።

ለእያንዳንዱ ቤት ሰሪ 70 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሁም ለጋራ መኖሪያ ቤት የሚሆን አማራጭ እንደሚዘጋጅ ገልጸዋል።

"የእድሉ ተጠቃሚዎች በሚኖሩበት ከተማ ሁለት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆናቸው፣ በስማቸው የተመዘገበ መኖሪያ ቤት የሌላቸውና የመንግስት ግብር ከፋይ መሆን ይጠበቅባቸዋል" ብለዋል ።

የሃገር መከላከያ ሰራዊት፣ የፌደራልና የልዩ ኃይል የማረሚያ ቤትና መደበኛ የፖሊስ  ሰራዊት አባላት በልዩ ሁኔታ የሚስተናገዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በመቀሌ በሐወልቲ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አበባ ኃይሌ ከዚህ በፊት  የቤት መስሪያ ቦታ ሳያገኙ መቆየታቸውን ገልጸው ዘንድሮ በማህበር ተደራጅተው ቤት ለመስራት መመዝገባቸውን ተናግረዋል ።

 "መኖሪያ ቤት ለመስራት  በማህበር መደራጀቴ አስደስቶኛል" ያሉት ደግሞ በቀዳማይ ወያነ ክፍለ ከተማ የሰላም ቀበሌ ነዋሪው አቶ አማኑኤል በርሄ ናቸው፡፡

ተደራጅተን በመቆጠብ የራሳችን መኖሪያ ቤት በመስራት ከኪራይ መላቀቅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

የክልሉ ፍትህ ቢሮ ቤት ሰሪዎችን የማደራጀትና የመመዝገብ ኃላፊነት የተሰጠው መሆኑ ታውቋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም