ለገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ተነሺዎች የሶስት ቢሊዮን ብር ካሳ ተከፈለ - ኢዜአ አማርኛ
ለገናሌ ዳዋ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ተነሺዎች የሶስት ቢሊዮን ብር ካሳ ተከፈለ
ጎባ የካቲት20/2011 ለገናሌ ዳዋ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ከቄያቸው የተነሱ የመዳወላቡ ወረዳ ነዋሪዎች የካሳ ክፍያ ቅሬታቸው በመፈታቱ መደሰታቸውን ገለጹ፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል በበኩሉ ከ5ሺህ ለሚበልጡ የልማት ተነሺዎች ሶስት ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የካሳ ክፍያ መፈጸሙን አስታውቋል።
ከመዳ ወላቡ ወረዳ የልማት ተነሺዎች መካከል ሼህ ከድር ሀሰን በሰጡት አስተያየት ለፕሮጀክቱ ግንባታ የእርሻ ይዞታቸውን ቢያስረክቡም ካሳ ሳይከፈላቸው ለአምስት ዓመታት በመዝግየቱ ለሚመለከተው አካል ቅሬታቸውን ስያቀርቡ ቆይተዋል።
“በአሁኑ ወቅት ቅሬታዬ ሰሚ በማግኘቱ ይዞታዬንና ንብረቴን መሰረት ያደረገ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ በማግኘቴ ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡
ገንዘቡን የባንክ ሂሳብ ደብተር ከፍተው ማስቀመጣቸውን የሚናገሩት ሼህ ከድር በቀጣይ አዋጭ በሆነ ኢንቨስትመንት ለመሰማራት ቅድመ ዝግጅት እያደረጉ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ሌላው የወረዳው ልማት ተነሺ አቶ ኡስማን አብዳ በበኩላቸው እንደገለጹት ከአሁን በፊት በአካባቢያቸው ለግዙፍ ልማት ፕሮጀክቶች ከይዞታቸው ለሚነሱ አርሶ አደሮች የሚፈጸመው የካሳ ክፍያ ግምት ተነሺዎችን ያላማከለ በመሆኑ ቅሬታ ሲያስከትል ቆይቷል።
ለኃይል ማመንጫው ፕሮጀክት የልማት ተነሺዎች የተፈጸመው የካሳ ክፍያ ፍትሃዊ በመሆኑ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው የልማት ተነሺዎች ደስተኛ መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ኡስማን ገለፃ በካሳ ክፍያ የደረሳቸውን ሁለት ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ አዋጭ በሆነ የልማት ስራ በመሰማራት የራሳቸውንና የቤተሰባቸውን ህይወት ለመለወጥ ተነሳስተዋል።
“መንግስት ለዓመታት ስናቀርብ የነበረውን የካሳ ክፍያ ቅሬታ ተቀብሎ መፍታቱ የህዝብን ጥያቄ ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የገባውን ቃል በተግባር ያሰየበት ነው” ያሉት ደግሞ ሌላኛዋ የልማት ተነሺ ወይዘሮ መንደሪና አህመድ ናቸው።
በካሳ ያገኙትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንዲችሉ መንግስት በገንዘብ አጠቃቀምና ቁጠባ ላይ ያተኮረ ግንዛቤ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።
ፕሮጀክቱ በአካባቢያቸው መገንባቱ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ በመሆኑ ለተፈጻሚነቱ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የመዳ ወላቡ ወረዳ ምክትል ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱነሲር ሁሴን በበኩላቸው ከፕሮጀክቱ ጋር ተያይዞ በወረዳቸው 3 ሺህ 258 አባወራዎች ከእርሻ ይዞታቸው ተነስተዋል።
በየደረጃው የሚገኙ ባለድርሻ አካላት ከካሳ ክፍያው ጋር ተያይዞ ሊጣሩ የሚገቡ ቅድመ-ሁኔታዎችን ከጣሩ በኋላ የወቅቱን የገበያ ሁኔታ ያገናዘበ የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሃይል የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞጎስ መኮንን በበኩላቸው “ለፕሮጅክቱ ግንባታ 5 ሺህ 29 የጎሮዶላና የመዳወላቡ ወረዳ ነዋሪዎች ተነስተዋል”ብለዋል፡፡
አስፈላጊ የሆኑ የሰነድና ሌሎች ቅድመ-ሁኔታዎች ከተጣሩ በኋላ መስፈርቱን ማሟላታቸው ለተረጋገጠ 95 በመቶ ለሚሆኑ የልማት ተነሺዎች 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የካሳ ክፍያ መፈጸሙን ጠቁመዋል።
ቀሪዎቹ አስፈላጊውን ቅድመ ሁኔታ ያላሟሉ 249 ተነሺዎች ክፍያ አለመፈጸሙን የገለጹት ደይሬክተሩ “ሰነዶችን ሟሟላታቸው ሲረጋገጥ በቀጣይ የካሳ ክፍያው ይፈጸምላቸዋል” ብለዋል።
የገናሌ ዳዋ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በኦሮሚያ ክልል በባሌና ጉጂ ዞኖች በሚገኙ የመዳ ወላቡና ጎሮዶላ ወረዳዎች አዋሳኝ ቦታ ላይ የተገነባ ሲሆን የፕሮጀክቱ የግንባታ አፈጻጸምም 97 ነጥብ 7 በመቶ ላይ ይገኛል” ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ፕሮጀክቱ በቅርቡ ተጠናቆ ለአገልግሎት ሲበቃ 254 ሜጋዋት ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።