ሚኒስቴሩ በፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ማዕከላትን ለመገንባት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ፈረመ

139

አዲስ አበባ የካቲት 20/2011 የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ስቲም ፓወር ከተሰኘ ተቋም ጋር በፈጠራና ቴክኖሎጂ ዘርፎች አብሮ ለመስራት የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሟል፡፡

ስምምነቱ በኢኖቬሽን ልማትና ማዕከላት ግንባታ፣ በቴክኖሎጂ የስራ እድል ፈጠራ እና የፋይናንስ ድጋፍን የሚያካትት ሲሆን የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንዲሁም  የኢኖቬሽንና የምርምር ሥራዎችን በጋራ ለመስራት የሚያስችል ነው፡፡

ስቲም ፓወር የተሰኘው ተቋም ተማሪዎች በሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ በኢንጂነሪንግ እና ሂሳብ ትምህርቶች ብቁና ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ከንድፈ-ሃሳብ ትምህርት በዘለለ በተግባር እንዲማሩ የሚያስችል ማዕከል በዩኒቨርሲቲዎች እየገነባ ነው።

ስምምነቱን የፈረሙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሹመቴ ግዛው እና የስቲም ፓወር ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ቅድስት ገብረአምላክ ናቸው።

ስቲም ፓወር በቡራዩ ለሚገነባው የኢኖቬሽን እና ምርምር ማዕከል ግብዓት የሚሆኑ የኢኖቬሽን ስራዎች ማበልፀጊያ ቁሳቁሶች ድጋፍም አድርጓል፡፡

ስቲም ፓወር ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርቡ የተማሪዎችን የሳይንስና ቴክኖሎጂ አቅም ማሳደግ የሚያስችል በ7 ዩኒሸርሲቲዎች የቴክኖሎጂ ማዕከላት ለመገንባት ውል መግባቱ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም