የአንድ ቤተሰብ ሰባት ሰዎችን ህይወት ያጠፋው የግንብ መደርመስ

29

መቱ የካቲት 20/2011 በኢሉአባቦር ዞን መቱ ከተማ በደረሰ የግንብ አጥር መደርመስ የአንድ ቤተሰብ ሰባት ሰዎች ሕይወት ማለፉ ነው የተነገረው፡፡

የአካባቢው ፓሊስ እንደገለፀው የሰዎቹ ሕይወት ሊያልፍ የቻለው በከፍታ ተሰርቶ የነበረው አንድ የንግድ ድርጅት የግንብ አጥር በጎረቤት መኖሪያ ቤት ላይ ድንገት በመደርመሱ ነው።

በአደጋው በእንቅልፍ ላይ የነበሩ እናትና ስድስት ልጆቻቸው ሕይወት ወዲያውኑ አልፏል።

ሕይወታቸውን ካጡ የቤተሰቡ አባላት አምስቱ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆኑ ታዳጊ ህጻናት ናቸው፡፡
የሟቾቹ ጎረቤቶች እንደተናገሩት የቤተሰቡ አባላት በአነስተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙና በቀን ሥራ የሚተዳደሩ ነበሩ፡፡

የቀን ሥራ እየሰራ ቤተሰቦቹን ሲያስተዳድር የነበረው የቤቱ አባወራ ከዓመት በፊት በሕመም ምክንያት ሕይወቱ ማለፉ ታውቋል ፡፡
የመቱ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት የወንጀል ምርመራና ፍትህ አሰጣጥ ሥራ ሂደት መሪ ኮማንደር ተሾመ ታደሰ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው ትላንት ከሌሊቱ 8፡00 ሰዓት ላይ የደረሰው በከተማው ቀበሌ 01 ውስጥ ነው፡፡
ኮማንደር ተሾመ እንዳሉት የድርጅቱ ባለቤት በቁጥጥር ስር ውለው የአደጋው መንስኤም በመጣራት ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም