የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነባር ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም እሰራለሁ--ደኢህዴን - ኢዜአ አማርኛ
የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነባር ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም እሰራለሁ--ደኢህዴን
ሀዋሳ የካቲት 19/2011 በክልሉና ከክልሉ ውጪ የተፈጠሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ነባር ባህላዊ እሴቶችን በመጠቀም እንደሚሰራ የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ/ደኢህዴን አስታወቀ።
የደኢህዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ካለፈው ረቡዕ ጀምሮ በአርባምንጭ ከተማ ሲያካሄድ የነበረውን ጉባኤ ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት አጠናቋል።
የማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤቱ በአስረኛው ድርጅታዊ ጉባኤ አቅጣጫዎች አፈጻጸም ላይ ያደረገውን የስድስት ወራት ግምገማ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ እንዳመለከተው እንደሀገር የተጀመረው የለውጥ እንቅስቃሴ ጥልቅና ሁሉንም ህዝብ የሚጠቅም ነው።
ለውጡ ካመጣው ተስፋ በተቃራኒ ሥጋቶችም የተጋረጡበት እንደሆነ አመልክቶ ድርጅቱ ክልሉን ለስጋት የዳረጉ ድክመቶችን በመለየት የህዝቡን የልማት ፣ የመልካም አስተዳደር ፣ የአደረጃጀትና ሌሎች አዳጊ ፍላጎቶችን ለመመለስ ወደ ተግባር መግባቱን ጠቁሟል።
በፌዴራል ስርዓት የህዝቦች ራስን በራስ የማስተዳደር፣ የእኩልነትና የፍትሃዊ ተጠቃሚነት እንዲሁም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ በነፃነት የመስራት መብቶች በትክክለኛ ገፅታና በተሟላ መንገድ እንዲከበሩ እንደሚሰራም አመልክቷል።
ህብረ-ብሄራዊነትን ለመናድ የሚነሳ የትኛውም ኃይል የብሄር ብሄረሰቦችን እና የሀገሪቱን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ድርጅቱ በግንባር ቀደምትነት እንደሚታገለው ገልጿል።
አሁን በክልሉ የሚነሳው ክልል ሆኖ የመደራጀት ጥያቄ መላውን የክልሉን ህዝብ በሚጠቅም ሁኔታ በተረጋጋና መፍትሄ በሚያመጣ መንገድ በድርጅቱ መመራት እንዳለበት መግባባት ላይ መደረሱንም በመግለጫው አስታውቋል፡፡
የተጀመረውን የለውጥ ፍላጎት መምራት የሚችሉ ምሁራንን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን ማዕከል ያደረገ የምልመላና የግንባታ ስራ እንደሚጠናከር አመልክቶ የግብርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሳደግ ወጣቱ ወደ ምርት ተግባር እንዲገባ በብቃት መመራት እንዳለበትም ጠቁሟል።
በክልሉ ሰላም ለማምጣት የሀገር ሽማግሌዎች፣ ወጣቶችና ሴቶች ያበረከቱት አስተዋፆኦ ከፍተኛ መሆኑን ያመለከተው መግለጫው በቀጣይነትም ዘላቂ የሆነ ሰላም እና ፀጥታን ለማስፈን ህብረተሰቡ በጋራ የመኖር እና የአብሮነት እሴቱን እንዲያጠናክር ጠይቋል።
ሌብነት፣ ሙስናና ብልሹ አሰራሮችን በየደረጃው ፈትሾ አስተማሪ እርምጃዎችን በመውሰድ ሂደት ከህዝብ ጋር ግልፀኝነትን ፈጥሮ መንቀሰቀስ እንደሚገባ የተቀመጠ ቢሆንም የተሰሩ ስራዎች በቂ አለመሆናቸው እንደተገመገመም አስታውቋል።
በከልሉም ሆነ በሀገር አቀፍ ደረጃ በሰላማዊ መንገድ ተመዝግበው ከሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የህዝቦችን የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ ድጋፍና ትብብር በማድረግ ትኩረት ሰጥተን እንሰራለን ብሏል መግለጫው።
በአርሶና አርብቶ አደሩ ህይወት የሚመጣው ለውጥ ለገጠር ትራንስፎርሜሽን ግብ ስኬት ብሎም ለከተሞች ልማትና ወደ ኢንዱስትሪ ግስጋሴ ያለውን ወሳኝነት በመረዳት በዘርፉ የሚስተዋሉ አደናቃፊ አሰራሮችና ማዕቀፎችን ፈትሾ በማስተካከል የሚሰራ መሆኑንም አመልክቷል።
በአርብቶ አደር አካባቢ ለመንደር ማሰባሰብ አስፈላጊ የሆኑ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት እና ያሉ የመስኖ አውታሮችን የማጎልበት ስራ በትኩረት ይፈጸማል ብሏል በመግለጫው።