ቀጥታ፡

የሉሲ ቅሪተ አካል ጂግጂጋ ገባ

ጂጋጂጋ የካቲት 19/2011 የሉሲ/ድንቅነሽ/ ቅሪተ አካል ዛሬ ጂግጂጋ  ከተማ ሲገባ  ደማቅ አቀባባል ተደረገለት፡፡

“ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር” በሚል ከአዲስ አበባ ተነስቶ ሰመራ ከደረሰ በኋላ ዛሬ ጂግጂጋ ከተማ ለገባው  የሉሲ/ድንቅነሽ/ ቅሪተ አካል አቀባበል የተደረገለት ጅግጅጋ ገራድ ዊልዋል አውሮፕላን ማረፊያ ነው።

ቅሪተ አካሉን ይዘው የመጡት የ“ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር” ልዑካን ቡድን አባላት በኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ነው፡፡

ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን ያረጋገጠው የሉሲ ቅሪተ አካል ይዘው በመጡት የልዑካን ቡድን አባላት አቀባበል ስነስርዓት ወቅት  የክልሉ መንግስት አመራሮች፣ የጎሳ መሪዎች፣የእምነት አባቶች የክልሉ ፖሊስ ማርሽና የባህል ቡድን አባላት በመገኘት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ሰላድ ደበር የድንቅነሽ ጉዞ በጅግጅጋ ቆይታዋ ያማረ እንዲሆን በቂ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

“ጉዞ ሉሲ ለሰላምና ለፍቅር” በሚል መርሃ-ግብር ቅሪቱ አካሉ ነገ ለህዝብ እይታ ክፍት እንደሚሆን ገልጸዋል፡፡

የሉሲ ቅሪተ አካል በክልሎች ተዘዋውሮ እንዲታይ መደረጉ በኢትዮጵያ ምድር ፍቅርና ሰላም እንዲነግስ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል፡፡

በአፋር ክልል አዋሽ ሸለቆ ውስጥ በሚገኝ ሃዳር በተሰኘ አካባቢ የተገኘው የሉሲ ቅሪተ አካል ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መገኛ ምድር መሆኗን አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም