በሳዑዲ አረቢያ ያለመኖሪያ ፈቃድ ይኖሩ የነበሩ 600 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ - ኢዜአ አማርኛ
በሳዑዲ አረቢያ ያለመኖሪያ ፈቃድ ይኖሩ የነበሩ 600 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ
አዲስ አበባ የካቲት 19/2011 በሳዑዲ አረቢያ ያለ መኖሪያ ፈቃድ ይኖሩ የነበሩ 600 ኢትዮጵያውያን ዛሬ ወደ አገራቸው ተመለሱ።
ስደተኞቹ ወደ አገራቸው የተመለሱት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጅዳ ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት፣ ከሳዑዲ አረቢያ መንግስት እና ከዓለም አቀፍ የፍልሰተኞች ድርጅት (አይ ኦ ኤም) ጋር በመተባበር ነው።
መንግስት በመካከለኛው ምስራቅ እና በተለያዩ አገሮች ችግር ያጋጠማቸውን ዜጎች ወደ ትውልድ አገራቸው የመመለሱን እንቀስቃሴ አጠናክሮ መቀጠሉን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አመልክቷል።
በዚህም መሰረት በየአገሮቹ ባሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና አይ ኦ ኤም እንዲሁም ከየአገሮቹ ጋር በመተባበር ዜጎች መብታቸው ተጠብቆና ተከብሮ በፍቃዳቸው ወደአገራቸው የመመለሱን ስራ አጠናክሮ መቀጠሉን ነው መግለጫው ያመላከተው።
ያለህጋዊ መኖሪያ ፍቃድ በሳኡዲ የሚኖሩ የሌሎች አገራት ዜጎች አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ እንደ አውሮፓዊያን አቆጣጠር ሚያዚያ 2017 ህግ ማውጣቷ ይታወሳል።
ከዚሀን ጊዜ ጀምሮም ከ230 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ከሳኡዲ አረቢያ መመለሳቸውን የዓለም ዓቀፉ ፍልሰት ድርጅት መረጃ ይጠቁማል።