ቀጥታ፡

ሰው ገጭተው ባመለጡ አሽከርካሪዎች ለደረሰ ጉዳት የከፈልኩት ካሳ ባለመመለሱ ህልውናዬ አደጋ ተጋርጦበታል - የመድህን ፈንድ

አዲስ አበባ የካቲት 19/2011ሰው ገጭተው ባመለጡ አሽከርካሪዎች ለደረሰ ጉዳት የከፈለው ካሳ በወቅቱ ባለመመለሱ ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁን የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ገለፀ።

ኤጀንሲው ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ ሰዎችን ገጭተው ባመለጡ አሽከርካሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው 294 ሰዎች ከ8 ሚሊዮን ብር በላይ ካሳ ከፍሏል፤ ያም ሆኖ ከዚህ ውስጥ ማስመለስ የተቻለው ከአንድ አሽከርካሪ ብቻ ነው። 

በርካታ አሽከርካሪዎች ሰዎችን ገጭተው የሚያመልጡት በአዲስ አበባና ዙሪያዋ ባሉ ከተሞች እንደሆነ የኤጀንሲው መረጃ ያመለክታል።   

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በበኩሉ ሰዎችን ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎች ቁጥር በተለይ በምሽት እየተበራከተ የመጣ በመሆኑ የሌሊት ቁጥጥር ለመጀመር ዕቅድ እንዳለው ገልጿል።

ገጭተው ባመለጡ አሽከርካሪዎች የተጎዱ ሰዎችም ከአደጋው በኋላ በአፋጣኝ ወደህክምና ተቋም ባለመሄዳቸው ለከፋ ችግር እንደተጋለጡም አስረድተዋል።

በአሽከርካሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦች ከኤጀንሲው የካሳ ክፍያ ቢያገኙም አሽከርካሪዎች በሰው ላይ ጉዳት አድርሰው ከማምለጥ ይልቅ የተጎዳውን ሰው ወደ ህክምና ተቋም ቢያደርሱ ህይወት የማትረፍ ዕድል እንደሚኖርም ገልጸዋል። 

ወይዘሮ ብዙነሽ አንጀሎ የተባሉ ነዋሪ "የ26 አመት ወጣት ዛሬ እሱን አጥቻለሁ ዓይኔም ጠፍቷል ባለቅስም ምን ባደርግም ምንም ተሰሚነት የለኝም የገጨም አልተያዘም ዝም ብዬ ነው የምዋልለው ስድስት ወር ሙሉ 40 ሺህ ብር ተሰጥቶኛል" ብለዋል፡፡

ወይዘሮ ሙሉነሽ ተስፋዬ የተባሉት ሌላዋ ነዋሪ ደግሞ "ዶሮ እንኳን ያሳሳሻል እንኳን የሰው ልጅን ያህል ነገር ጥለው ገድለው ሲሄዱ ለእነሱስ ምን አይነት ስሜት ይሰማቸዋል፡፡”

በወቅቱ አንስቶት ቢሄድ ኖሮ ይድንልኝ ነበር ሰላላነሳው ነው ደሙ ፈሶ አልቆ ለሞት የበቃው።”ብለዋል፡፡

በቀለች ካባ የተባሉ ሌላ አስተያየት ሰጪ እንዳሉት በኤጀንሲው በኩል ለደረሰባቸው አደጋ የገንዘብ ድጋፍ ቢደረግላቸውም  ቋሚ የአካል ጉዳት ገጥሟቸዋል። በአከርካሪ አጥንታቸው ላይ ብረት በመገጠሙ እንደልብ መንቀሳቀስና መስራት እንዳቃታቸውም ጠቅሰዋል።   

መርካቶ ከምሽቱ 3 ሰዓት ገጭቷቸው እንደሄደ  ነው የሚናገሩት  ራሴን አላውቅም አጋጣሚ ስልክ ቦርሳዬ ውስጥ ነበረ ለእህቴ ተደወለላትና ኮሪያ ሆስፒታል ወሰደችኝ ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ በበኩሉ ሰዎችን ገጭተው ባመለጡ አሽከርካሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ካሳ እንደከፈለ ገልጿል።

በኤጀንሲው የመድህን ኦፕሬሽን ዳይሬክተር አቶ አዲል አብዱላሂ እንዳሉት ኤጀንሲው ሰዎችን ገጭተው ባመለጡ 294 እና ሦስተኛ ወገን መድህን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት ለደረሰባቸው 33 ሰዎች ካሳ ከፍሏል።

ኤጀንሲው ለአንድ ተጎጂ እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ ካሳ የሚከፍል ሲሆን አስካሁንም 8 ሚሊዮን ብር ለካሳ ክፍያ ወጪ አድርጓል፤ የተመለሰው ግን ከአንድ አሽከርካሪ ብቻ ነው ብለዋል። ይህ ገንዘብ  በወቅቱ ተመላሽ ሳይሆን በዚሁ ከቀጠለ የተቋሙ ህልውና አደጋ ውስጥ እንደሚወድቅ አቶ አዲል አብራርተዋል።

አብዛኛዎቹ አሽከርካሪዎች ገጭተው የሚያመልጡት በአዲስ አበባና በዙሪያዋ መሆኑን የገለጹት አቶ አዲል በዚህ ሳቢያ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ ለህክምና ተቋማት የቴክኒክ ስልጠና መሰጠቱን አብራርተዋል።

ኤጀንሲው ባደረገው የዳሰሳ ጥናት በርካታ አደጋዎች የሚደርሱት ከምሽት ሦስት ሰዓት በኋላ ሲሆን በትራፊክ ፖሊስ በኩል ያለው የምሽት ቁጥጥር የላላ መሆኑን አንስተዋል፤ አደጋው የሚከሰተው የአልኮል መጠጥና እፆችን ተጠቅመው በሚያሽከረክሩ ግለሰቦችም ጭምር እንደሆነ መረጋገጡን አስረድተዋል። 

በቀጣይ አደጋ አድርሰው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን ለመቆጣጠር ፖሊስ በካሜራ የታገዘ የቁጠጥር ስራ ሊያከናውን እንደሚገባ ኀብረተሰቡም ከፖሊስ ጋር በመተባበር አደጋ የሚያደርሱ አሽከርካሪዎችን ማጋለጥ እንዳለበት ተናግረዋል።

ፖሊስን ጨምሮ ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ኤጀንሲው በቅንጅት እየሰራ እንደሆነ የገለጹት አቶ አዲል ሰው ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደረገውን ቁጥጥር ለማጠናከር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የኢንዶክትሪኔሽንና የህዝብ ግንኙነት ምክትል ዳይሬክተር ኮማንደር ፋሲካ ፋንታ በበኩላቸው ሰው ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን በሰው ኃይል ብቻ መቆጣጠር አስቸጋሪ በመሆኑ ኮሚሽኑና የፌዴራል ፖሊስ በከተማዋ የሲ ሲ ቲቪ ካሜራ እንዲገጠም እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል።

የወንጀል መከላከል ስራውን በቴክኖሎጂ እንዲታገዝ ከማድረግ በተጨማሪ በርካታ አደጋ የሚበዛው ሌሊት ስለሆነ ሰው ገጭተው የሚያመልጡ አሽከርካሪዎችን ለመያዝ በተመረጡ ቦታዎች የሌሊት ቁጥጥር ለመጀመር ዕቅድ እንዳለም ገልጸዋል።

በአሽከርካሪዎቹ ላይ የሚወሰደው የህግ ቅጣት የላላ መሆኑን የገለጹት ኮማንደር ፋሲካ ቅጣቱን ጠበቅ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ የቁጥጥር ስራውን አጠናክሮ የሚቀጥል ሲሆን ኀብረተሰቡም ለኮሚሽኑ ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።

የመድህን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ የተሽከርካሪ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች አስቸኳይ ህክምና በነፃ እንዲያገኙ የሚያደርግ ተቋም ነው።

እንዲሁም ባልታወቁና የሦስተኛ ወገን የመድህን ሽፋን በሌላቸው ተሽከርካሪዎች ጉዳት ለሚደርስባቸው ሰዎች ካሳ የሚከፍል ሲሆን ለካሳ ያወጣውን ወጪ አደጋ ያደረሱ አሽከርካሪዎች በህግ እንዲከፍሉ ያደርጋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም