የሀገራቸው መንግስት ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ልማት ድጋፉን እንደሚቀጥል የጃፓን አምባሳደር ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የሀገራቸው መንግስት ለኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ ልማት ድጋፉን እንደሚቀጥል የጃፓን አምባሳደር ገለጹ
ጎንደር የካቲት 19/2011 ኢትዮጵያ ለጤናው ዘርፍ ተደራሽነት እያከናወነች ያለውን ልማት የሀገራቸው መንግስት ድጋፉን እንደሚቀጥል በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ገለጹ፡፡
አምባሳደሩ በጃፓን መንግስትና በወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ትብብር በጎንደር ዙሪያ ወረዳ በአንድ ሚሊዮን 800ሺህ ብር ወጪ የተገነባውን ዘመናዊ የነፍሰጡር እናቶች ማዋለጃና የጨቅላ ህጻናት ማቆያ ማዕከል መርቀዋል፡፡
በምንዝሮ ጤና ጣቢያ ውስጥ የተገነባውን ማዕከል አምባሳደር ዳይሱኪማሱናጋ መርቀው ሲከፍቱ እንደተናገሩት የጃፓን መንግስት በኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ ለሚከናወን ልማት ቅድሚያ ሰጥቶ ድጋፍ እያደረገ ነው፡፡
ከዚህ ቅድሚያ ከሚሰጡት ውስጥ የእናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት መሆኑን ጠቅሰው በዘርፉ ለተቀረጹ ፕሮጀክቶች ባለፉት ሶስት ዓመታት በአማራ ክልል ለሚገኙ 14 ጤና ጣቢያዎች ከ49 ሚሊዮን ብር በላይ የጃፓን መንግስት ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
የጃፓን መንግስት በወርልድ ቪዥንና በሌሎችም መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች በኩል ማህበረሰብ ጠቀም የልማት ፕሮጀክቶችን እየደገፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አበባው ገበየሁ በበኩላቸው በክልሉ የእናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት ቅድሚያ ከተሰጣቸው የጤና ዘርፎች ግንባር ቀደም መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከጃፓን መንግስት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ በክልሉ አምስት ጤና ጣቢያዎች ውስጥ የእናቶችና ህጻናትን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያግዙ ማዕከላት ገንብቶ ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡
" በጎንደር ዙሪያ ወረዳና በደራ ወረዳዎች የተገነቡት ማዕከላት አሁን ላይ የእናቶችና ህጻናትን የጤና አገልግሎት በማሻሻል በኩል የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ናቸው "ብለዋል፡፡
"በዚህ ማዕከል ምረቃ ስነስርዓት በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር በመገኘታቸው ታላቅ ክብር ይሰማኛል" ያሉት ደግሞ የወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር ሚስተር ኤድዋርድ ብሮውን ናቸው፡፡
ለወርልድ ቪዥን ኢትዮጵያ ከፍተኛ የገንዘብ ድጋፍ ከሚያደርጉ የእስያ ሀገራት ጃፓን ግንባር ቀደም መሆኗን ሚስተር ኤድዋርድ ተናግረዋል፡፡
"ድርጅቱ በጤናው ዘርፍና በንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት በርካታ ፕሮጀክቶች ነድፎ እየሰራ ነው፤ ከ100ሺህ በላይ የህብረተሰብ ክፍሎችንም ተጠቃሚ ማድረግ ችሏል" ብለዋል፡፡
ከጎንደር ዙሪያ ወረዳ ነዋሪዎች መካከል ቄስ መላእከሰላም ገብረስላሴ በማዕከሉ ምረቃ ወቅት እንዳሉት ካሁን ቀደም እናቶች በቤት ውስጥ በመውለድ ህይወታቸው ያልፍ ነበር፡፡
" ዛሬ ላይ እናቶች በጤና ጣቢያ የመውለድ ግንዛቤአቸው እያደገ በመምጣቱ የበርካታ እናቶች ህይወት እየተረፈ ችግራቸውም እየተፈታ ነው" ብለዋል፡፡
በወረዳው የጤና ኤክስቴንሽን ሰራተኛ ወጣት ስመኝ መንግስቱ የማዕከሉ መከፈት የወላጆችን ሞት እንደሚቀንስ ገልጻ ጎንደር በመሄድ የሚደርስባቸውን እንግልትና ስቃይ እንደሚያስቀር ተናግራለች፡፡
ማዕከሉ የእናቶች ማቆያ የማዋላጃና የጨቅላ ህጻናት መከታተያ ክፍሎችን ያካተተ ሲሆን በቀን እስከ ስድስት የሚደርሱ ወላዶችን የማስተናገድ አቅም አለው፡፡
የማዕከላዊ ጎንደር ምክትል አስተዳዳሪ ለአምባሳደሩና ለወርድ ቪዥን ኢትዮጵያ ዋና ዳይሬክተር የሀገር ባህል አልባሳት ስጦታ አበርክተዋል፡፡