በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ እንዲሳተፍና መብቱ እንዲጠበቅ ይሰራል ተባለ - ኢዜአ አማርኛ
በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ በሀገሩ ጉዳይ እንዲሳተፍና መብቱ እንዲጠበቅ ይሰራል ተባለ
አዲስ አበባ የካቲት 19/2011 በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገራቸው ጉዳይ ያለምንም ልዩነት ለማሳተፍና ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ገለፀ።
የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ በቅርቡ መቋቋሙ ይታወሳል።
ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሆነው ይህ የፌደራል መስሪያ ቤት የቋቋመበትን ዓላማና የትኩረት መስኮች በተመለከተ ዛሬ መግለጫ ተሰጥቷል።
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በዚሁ መግለጫ እንዳሉት፤ ኤጀንሲው በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች መብትና ጥቅም የማስጠበቅ ተልዕኮ አለው።
በየትኛውም ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ያለምንም ልዩነት በሀገራቸው ጉዳይ በንቃት እንዲሳተፉ ማድረግ የኤጀንሲው ዋነኛ ግብ መሆኑንም አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ እንደ አገሮቹ ነባራዊ ሁኔታ ለሀገራቸው ሊሰጡት የሚችሉትን ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት የምንከተለው አሰራር የተለያየ ሊሆን ይችላል ብለዋል ዋና ዳይሬክተሯ።
ኤጀንሲው ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሀገር ውስጥ እንዳሉት ሁሉ በሀገራቸው ጉዳይ በንቃት በማሳተፍ መብትና ጥቅማቸውን እንደሚያስከብር ገልጸዋል።
ለዚህ ደግሞ የራሱ በጀት፣ አሰራርና አደረጃጀት እንዲኖረው ከማድረግም ባሻገር ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የሚሰራበት ህግ ማዕቀፍ መዘጋጀቱንም አክለዋል።
ዲያስፖራውን የማስተባበርና የመምራት እንዲሁም የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በተቀላጠፈ መንገድ ለማድረስ ዝግጅታቸውን እንደጨረሱ ገልጸዋል።
የኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ መሀመድ እንድሪስ በበኩላቸው ዲያስፖራውን ንቁ ተሳታፊ በማድረግ በሀገሩ ገብቶ መስራት የሚችልበትን እድል የማመቻቸት ተግባር ይከናወናል ብለዋል።
በውጭ የሚኖረው ኢትዮጵያዊያና ትውልደ ኢትዮጵያዊ ቁጥር በሚሊዮኖች የሚገመት ቢሆንም ኤጀንሲው በቅድሚያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ቁጥሩን በውል ማረጋገጥን ጨምሮ አጠቃላይ የዲያስፖራውን መረጃ ማሰባሰብ እንደሚሆን ተገልጿል።
ኤጀንሲውን ለማደራጀት የተለያዩ ተግባራት የተከናወኑ ሲሆን እስካሁን የ53 ሰራተኞች ቅጥር ተፈጽሟል ተብሏል። በተያዘው ዓመት ከ200 ሚሊዬን ብር በላይ በጀት ለኤጀንሲው ሥራ ማስኬጃ እንደተያዘም ተመልክቷል።
ኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ ማኅበረሰብን ጨምሮ የተለያዩ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የኤጀንሲውን ሥራ መጀመር የሚያበስር መርሃ-ግብር የካቲት 22 ቀን 2011 ዓ.ም በሸራተን አዲስ ሆቴል ተዘጋጅቷል።
የኢትዮጵያ መንግስት በውጭ የሚኖሩ ዜጎች በአገራቸው ልማት መሳተፍ ይችሉ ዘንድ የዲያስፖራ ትረስት ፈንድ ማቋቋሙም ይታወሳል።
በሚሊዮኖች የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን አውሮፓ፣ አሜሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅ አገራትን ጨምሮ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በተለያየ የሥራ መስክ ተሰማርተው ይገኛሉ።