ጋዜጠኛ ገብረእግዜአብሔር ገብረስላሴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ - ኢዜአ አማርኛ
ጋዜጠኛ ገብረእግዜአብሔር ገብረስላሴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
የካቲት 19/2011 በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በጋዜጠኝነትና በሌሎችም የሙያ ዘርፎች ለረጅም ዓመታት ያገለገለው ገብረእግዜአብሔር ገብረስላሴ ተስፋሁነኝ ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ።
አቶ ገብረእግዜአብሔር ከእናቱ ከወይዘሮ ለምለም አብረሃ ከአባቱ አቶ ገብረስላሴ ተስፋሁነኝ ህዳር 29 ቀን 1958 ዓ.ም በቀድሞ ትግራይ ክፍለ ሀገር ሽሬ አውራጃ ሰለክላካ ወረዳ እንደተወለደ የህይወት ታሪኩ ያስረዳል።
እድሜው ለትምህርት ሲደርስ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በአክሱም መካነየሱስ ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በአክሱም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሏል።
በቀድሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን ኢንስቲትዩት በህትመት ጋዜጠኝነት፣እንዲሁም በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ በዴቬሎፕመንት ኮሙዩኒኬሽንና በጋዜጠኝነት ሶስት ዲፕሎማ አግኝቷል፡፡
በኢዜአ አክሱም ቅርንጫፍ ከሚያዚያ 17/በ1978 ዓ.ም ጀምሮ አንደኛ ደረጃ ዜና ወኪል ሆኖ ሰርቷል፤ በኋላም ወደ አዲስ አበባ ተዛውሮ በዋናው መስሪያ ቤት የዜና ተቀባይና አስተላላፊነት እንዲሁም በተለያዩ የስራ ክፍሎች አገልግሏል፡፡
አቶ ገብረእግዜአብሔር ገብረስለሴ ተስፋሁነኝ በህመም ምክንያት በህክምና ቦርድ በ2008 ዓ.ም ጡረታ እንደወጣ ታውቋል።
ባደረበት ህመም በህክምና ሲረዳ ቆይቶ በተወለደ በ53 ዓመቱ ትናንት ከዚህ አለም በሞት የተለየው አቶ ገብረእግዜአብሔር ባለትዳርና የአንዲት ሴትና የአንድ ወንድ ልጆች አባት ነበር፡፡
የቀብር ስነ-ስርዓቱም ዛሬ ዘጠኝ ሰዓት ለቡ አካባቢ በሚገኘው በምስራቀ ፀሐይ ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን ይፈጸማል፡፡