የሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት አገራዊ የለውጥ ሂደቱን እንደግፋለን አሉ

75
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አገራዊ አንድነት ለማምጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንደሚደግፉ በሰሜን አሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያዊያን ተናገሩ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በውጪ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው አንድነትና ዕድገት የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ጥሪ ማድረጋቸው ይታወሳል። በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዲያስፖራው ያቀረቡትን ጥሪ በአዎንታ እንደሚመለከቱት ገልጸዋል። በሰሜን አሜሪካ የኢዜአ ወኪል እንደዘገበው ይህን ሃሳብ የሚገልጽ የአቋም መግለጫ በማውጣትም በአሜሪካ ለኢትዮጵያ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን አስረክበዋል። በአሜሪካ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን በአገራዊ ጉዳይ ላይ ለመምከር ከቀናት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ስብሰባ አካሂደዋል። በስብሰባው የታደሙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያንም፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እያከናወኑ ያለውን የለውጥ ሂደት ከዳር ለማድረስ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል። ከታዳሚዎቹ መካከል፤ ዶክተር ደረጄ በረደድ፤ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይዘውት የመጡትን አዲስ ተስፋ እውን ለማድረግ ሙሉ ድጋፍ እሰጣለው ብለዋል። የኢትዮ-አሜሪካ የዶክተሮች ቡድን ዋና ሥራ አስኪያጅ አማካሪ አቶ መላኩ ንጉሴ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ርብርብ እንደሚፈልግ ተናግረዋል። ከ300 በላይ አባላት ያሉትና ከ35 በላይ ልዩ የጤና ባለሙያዎችን የያዘው ቡድን በአዲስ አበባ ከተማ ዘመናዊ ሆስፒታል እየገነባ መሆኑን ገልጸው ይህም የትብብሩ ማሳያ ነው ብለዋል። ያም ሆኖ አሁንም በአገር ጉዳይ ላይ አንድ መሆንና ለጋራ እድገት መትጋት አስፈላጊ መሆኑን ነው የጠቆሙት። የዓለም አቀፍ የግብርናና የአካባቢ ምጣኔ ኃብት ባለሙያ ዶክተር ሻወል በትሩም "ለአገራችን የሚገባንን ለማድረግ ብሩሕ ተስፋ ይታየኛል " በማለት ነው አስተያየታቸውን የሰጡት። ይህም እድል በሁሉም የአገሪቱ ዜጎች እጅ ላይ እንዳለና ለዚህም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለአገሩ ሊሰራ እንደሚገባ አስረድተዋል። አገራዊ መነቃቃቱ ያለ ምንም እንቅፋት እንዲቀጥል የበኩላቸውን ለማድረግ ቃል የገቡበትን የአቋም መግለጫም ለአምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን አስረክበዋል። አምባሳደር ካሳም ኢትዮጵያውያንና ትውልደ-ኢትዮጵያውያን ለአገራችው ያደረጉትን ተግባር አድንቀው፤ መንግሥት ከጎናቸው እንደሚቆም ገልጸውላቸዋል። "በውጪ አገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ጉዳይ እንቅልፍ የሚያጡና ሁልጊዜ የሚያስቡ ናቸው" ሲሉም አምባሳደር ካሳ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም