ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ ፖሊሲ ሊኖራት ይገባል ተባለ

አዲስ አበባ  የካቲት 18/2011 ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ተቋም ኢትዮጵያ በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት የግሉን ዘርፍ የሚያሳትፍ ፖሊሲና የአሰራር ማዕቀፍ ሊኖራት እንደሚገባ ገለጸ።  

የአካባቢ፣ ደንና አየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ከኢጣሊያ የአካባቢ፣ መሬትና ባህር ሚኒስቴርና ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ተቋም ጋር በጋራ ያዘጋጀው የሁለት ቀን አውደ ጥናት በአዲስ አበባ ተጀምሯል።   

የአውደ ጥናቱ ዓላማ በአረንጓዴ ልማት ተሳትፎ ያላቸው የኢጣሊያ ኩባንያዎች ያላቸውን መልካም አጋጣሚ ለማስቃኘት ነው።  

ከአስር በላይ የኢጣሊያ ኩባንያዎች በታዳሽ ኃይል፣የተቀናጀ ፍሳሽ አወጋገድና ዘላቂ የውኃ ኃይል ልማት ላይ ያሉ አቅሞችና አማራጨችን  ለመዳሰስ እየተሳተፉ ነው። 

ዓለም አቀፉ የአረንጓዴ ልማት ተቋም የአፍሪካና የአውሮፓ ኃላፊ ዴክስፖስ አጉሪዴስ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግስት የአረንጓደ ልማትን አስፈላጊነት በቅጡ በመገንዘብ በእቅድ ውስጥ አካቶ መስራቱ የሚበረታታ ነው። 

ተቋሙ እኤአ ከ2010 ጀምሮ አገሪቷ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም አረንጓዴ ኢኮኖሚ ስትራቴጂ እንዲኖራት ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል።

በመሆኑም በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል የአቅም ግንባታ ድጋፍ እየተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ ያሉ አገራት በአረንጓዴ ኢኮኖሚ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ ቁልፍና ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑንም ኃላፊው ጠቅሰዋል።  

የግሉ ዘርፍ ሊሳተፍ የሚችልበት ፖለሲ ኢትዮጵያ ሊኖራት እንደሚገባ ገልጸው ተቋማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም አረጋግጠዋል።

የኢጣሊያ የአካባቢ፣ መሬትና የባህር ሚኒስቴር ተወካይ ብሩና ኮሃን በበኩላቸው ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት አረንጓዴ ልማቱ ላይ የሚሰሩ ሥራዎችን ለመደገፍ ቁርጠኛ አቋም አላት።  

በኢትዮጵያ፣ጅቡቲና ሱዳን የሚተገበር ፕሮጀክት በ11 ሚሊዮን ዩሮ ወጪ እየተተገበረ መሆኑን ገልጸው ከፕሮጀክቶቹ ውስጥ አምስቱ በኢትዮጵያ ስድስቱ ደግሞ በጅቡቲና በሱዳን የሚተገበሩ ናቸው። 

በተዳሽ ኃይል፣ በዘላቂ ውኃ አስተዳደር፣ በአየር ትንበያ ውጤታማነትና ከአየር ሁኔታ ጋር የሚስማማ የግብርና ስርዓት መዘርጋት ከትብብር መስኮቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።  

በኮሚሽኑ የኃብት ማፈላለግና ፕሮጀክት አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር አቶ ወርዲ ሐሺም በበኩላቸው ከኢጣሊያ መንግስት ጋር በመተባበር ከ7 ሚሊዮን ዶላር  በላይ በሆነ ወጪ የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል።     

በታዳሽ ኃይል ዘርፍ በሱማሌና በአፋር ክልሎች፣ በአየር ትንበያ ቅደመ ማስጠንቀቂያ፣ በውኃ፣ በኃይልና በቆሻሻ አወጋገድ ላይ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።    

በኢትዮጵያ ያሉ የግል ዘርፍ አንቀሳቃሾች በአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት በስፋት እንዲሳተፉ ይጠበቃል ያሉት አቶ ወርዲ አወደ ጥናቱ ለኢትዮጵዊያን የልምድ ልውውጥ መድረክ መሆኑን ገልጸዋል። 

በአገሪቷ በኃይል ልማት፣ በዘላቂ የውሃ ሃብትና በተቀናጀ ቆሻሻ አወጋገድ ላይ ለሚሳተፉ የግል ባለሃብቶች መንግሥት አስፈላጊውን ማበረታቻዎች ይሰጣልም ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም