በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ከቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች መሰረታዊ የጤና አገልግሎት እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 18/2011 በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ለተፈናቀሉና አደጋ ለደረሰባቸው ዜጎች መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት እየቀረበ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለፀ።
የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በየነ ሞገስ ለኢዜአ እንደገለፁት ተፈናቃዮቹ በአንድ ቦታ በብዛት በሚሰፍሩበት ወቅት ወረርሽኝ እንዳይከሰት አስቀድሞ የመከላከል ስራ እየተከናወነ ነው።
በተለይም ክትባት መስጠትን፣ ውሃ ማከምንና ጊዜያዊ መጸዳጃ ቤቶች መገንባትን ጨምሮ በሽታ የመከላከል ተግባር ይከናወናልም ብለዋል።
ዜጎች በተለያየ ምክንያት ተፈናቅለው ወደሌላ አካባቢ ሲሰደዱ ከሚያጋጥሙ ችግሮች መካከል አንዱ በቂ የጤና አገልግሎት እጦት መሆኑን ዶክተር በየነ ገልፀዋል።
በዚህ የተነሳ ተፈናቃዮች ችግር እንዳይገጥማቸው መሰረታዊ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።
ኢንስቲትዩቱ ተፈናቃዮች ባሉባቸው አካባቢዎች ባለሙያዎችን ማሰማራትን ጨምሮ የመድሃኒትና የህክምና ቁሳቁስና ሌሎች ግብኣቶችን እያቀረበ ነው ሲሉም ገልፀዋል።
በተጨማሪም ተፈናቃዮች በሚኖሩባቸው የዞንና የወረዳ የጤና ተቋማትም የስራ ማስኬጃ የገንዘብ ድጋፍ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።
ተፈናቃዮች በሚገጥማቸው ጊዜያዊ ችግሮች ምክንያት ለአእምሮ ጤና መታወክ እንዳይዳረጉም የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑንም ገልጸዋል።
በሌላ በኩል በግጭቶችና ሌሎችም ምክንያት የተቃጠሉ፣ የተዘረፉና የፈረሱ የጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የዳሰሳ ጥናት እየተደረገ እንደሆነም ጠቅሰዋል።