በጎንደር ከተማ ለሰርግ በተተኮሰ ጥይት የሙሽሪት ህይወት አለፈ

ጎንደር የካቲት 18/2011 በጎንደር ከተማ አስተዳደር በአዘዞ ክፍለ ከተማ በሰርግ ስነ-ስርዓት ላይ ለደስታ በተተኮሰ ጥይት የሙሽሪት ህይወት ሲጠፋ በሙሽራው ላይ የመቁሰል አደጋ መድረሱን ፖሊስ አስታወቀ።

በትናትናው ዕለት በክፍለ ከተማው እየሱስ አካባቢ ተብሎ በሚጠራው ቦታ በነበረ የሰርግ ስነ-ስርዓት ላይ መሆኑን የ5ኛ ፖሊስ ጣቢያ ሃላፊ ኮማንደር አስራቴ ባየ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡

ሃላፊው እንደገለፁት አደጋውን ያደረሰው የሙሽሪት የቅርብ ዘመድ ነው፡፡

እግሩ ላይ የመቁሰል አደጋ ያጋጠመው ሙሽራው በአሁኑ ወቅት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑንም  ኮማንደሩ ጠቁመዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ የያዘው የጦር መሳሪያ ህጋዊ ቢሆንም ሰሞኑን በአካባቢው የተጣለውን ክልከላ የተላላፈ ነው።

ህዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የጦር መሳሪያ ይዞ ያለመንቀሳቀስና ያለ አግባብ ጥይት የመተኮስን ገደብ በመተላለፍ በደስታ ላይ የሀዘን ድባብ እንዲፈጥር ግለሰቡ ህገ-ወጥ ድርጊት መፈጸሙን ተናግረዋል፡፡

ድርጊቱን የፈፀመው ግለሰብ በጊዜው ያልተያዘ ቢሆንም ፖሊስ አስፈላጊውን ክትትል በማድረግ ለህግ የማቅረብ ስራ እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

“በሰርግም ሆነ በለቅሶ ስነ-ስርአት ማንኛውም የጦር መሳሪያ የታጠቀ ግለሰብ ይዞ መገኘት የለበትም”ያሉት ኮማንደሩ በጦር መሳሪያ አያያዝና አጠቃቀም ዙሪያ ጥንቃቄ ሊደረግ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም