ቀጥታ፡

በሰሜን ሸዋ ዞን በተሻሻሉ የግብርና አሰራሮች ምርታማነትን ከእጥፍ በላይ ማሳደግ ተችሏል

ደብረ በርሃን  ግንቦት 21/2010 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችንና ግብአቶችን ተጠቅሞ እንዲያለማ በመደረጉ ምርታማነትን ከዕጥፍ በላይ ለማሳደግ መቻሉን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ። በመምሪያው የግብርና ኤክስቴሽን ኮሙዩኒኬሽን ቡድን መሪ አቶ ታለ አለምነው ለኢዜአ እንዳስታወቁት ባለፉት ዘጠኝ ዓመታት በተሰሩ ሥራዎች ከ688 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል። አርሶ አደሩ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ከመጠቀም ባለፈ በመስመር እንዲዘራና ምርቱን ለመሰብሰብ ኮምባይነር እንዲጠቀም ማድረግ መቻሉን አመልክተዋል። በዚህም በተለያዩ ሰብሎች ከሚለማው ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት ቀደም ሲል በዋና ዋና ሰብሎች 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ይገኝ የነበረው  ወደ 16 ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል። በሄክታር የሚሰበሰበው የምርት መጠንም 13 ነጥብ 7 ከመቶ ወደ 34 ከመቶ በማሳደግ የአርሶ አደሩን ተጠቀማነት ማረጋገጥ እንደተቻለ አቶ ታለ አስረድተዋል። የአርሶ አደሩን ምርታማነት ማሳደግ ብቻ ሳይሆን ለፋብሪካዎች ግብዓት የሚሆኑና ለውጭ ንግድ የሚውሉ ምርቶችንም በብዛትና በጥራት የማምረት ሥራ እየተለመደ መምጣቱን ነው የገለጹት። በተለይ ማሾ፣ የቢራ ገብስ፣ የዳቦና የማካሮኒ ሰንዴ ለፋብሪካ የሚቀርቡ ተጠቃሽ ምርቶች መሆናቸውን ቡድን መሪው አስታውቀዋል። በሰሜን ሸዋ ዞን ሞረትና ጅሩ ወረዳ ቦሎ ቀበሌ አርሶ አደር አደመ ጋሻው እንዳሉት ከአስር ዓመት በፊት የተሻሻለ የግብርና አሰራር ተጠቃሚ ባልነበሩበት ወቅት ከአንድ ሄክታር ተኩል መሬታቸው የሚያገኙት ምርት ለዓመታዊ የቤተሰብ ቀለብ አይበቃም ነበር። ባለፉት ዓመታት በአካባቢያቸው የተመደቡ የግብርና ባለሙያዎች በሰጧቸው ሙያዊ ምክር ታግዘውና በቂ ማደበሪያና ምርጥ ዘር ተጠቅመው በማልማታቸው በአሁኑ ወቅት በሄክታር እስከ 60 ኩንታል ስንዴ ማምረት መቻላቸውን አስታውቀዋል። በየዓመቱ ከሚያገኙት ገቢም ከቤተሰብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ከምርት ሽያጭ ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የገለጹት። በሲያ ደብርና ዋዩ ወረዳ የአገኝ ከልበሊ ቀበሌ አርሶ አደር ግርማ ቦጋለ በበኩላቸው የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተጠቅመው ማልማት በመጀመራቸው ቀደም ሲል በሄክታር አምስት ኩንታል ያገኙ የነበረው የስንዴ ምርት ወደ 40 ኩንታል ማሳደጋቸውን ተናግረዋል። "ከዓመታት በፊት በሄክታር ከ15 አስከ 25 ኩንታል አገኝ የነበረው የማሽላ ምርት በአሁኑ ወቅት አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከ50 እስከ 60 ኩንታል ምርት እያገኘሁ ነው" ያሉት ደግሞ በዞኑ ቀወት ወረዳ የኤለን ቀበሌ አርሶ አደር ደጀኔ ኃይሉ ናቸው። ከመኽር አርሻ በተጨማሪ በበጋ መስኖ ልማት በሄክታር ቀይ ሽንኩርት ከ250 ኩንታል በላይ በማምረት በአማካይ ከ60 ሺህ ብር በላይ ገቢ እያገኙና ኑሯቸውመ እየተለወጠ መሆኑን ጠቁመዋል። በባንክ ከ500 ሺህ ብር በላይ ገንዘብ መቆጠባቸውን የገለጹት አርሶ አደር ደጀኔ፣ በቅርቡ አንድ የህዝብ ማመላለሻ መኪና በመግዛት የትራንስፖርት አገልግሎት ለመጀመር ማቀዳቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም