ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የእጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊጉን እየመራ ነው
አዲስ አበባ የካቲት 18/2011 በኢትዮጵያ እጅ ኳስ ፕሪሚየር ሊግ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የደረጃ ተከታዩን ቂርቆስ ክፍለ ከተማን በማሸነፍ መሪነቱን አጠናከረ።
የፕሪሚየር ሊጉ 7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየምና በክልል ከተሞች ተካሄደዋል።
ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ቂርቆስ ክፍለ ከተማን 28 ለ 25 አሸንፏል።
ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ነጥቡን ወደ 14 ከፍ በማድረግ ከተከታዩ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ወደ ሦስት ከፍ አድርጓል።
ኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ በፕሪሚየር ሊጉ እስካሁን ያደረጋቸውን ሰባት ጨዋታዎች በማሸነፍ ስኬታማ ጉዞ እያደረገ ነው።
በአንጻሩ የአምናው የሊጉ አሸናፊ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ትናንት የሊጉን የመጀመሪያ ሽንፈት አስተናግዷል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በመጀመሪያው ክፍለ ጊዜ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበትና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ በአብዛኛው ኃይል ላይ ያመዘነ ጨዋታ ያሳየበት ነበር።
በሁለተኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ተዳክሞ የነበረ ሲሆን ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ የበላይነት በማሳየት ጨዋታውን ማሸነፍ ችሏል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ አሰልጣኝና የተወሰኑ ተጫዋቾች በዳኛ ውሳኔዎች ላይ ጠንከር ያለ ተቃውሞ ሲያቀርቡ የነበረ ሲሆን በተለይም ተጫዋቾቹ ቅሬታ ያቀረቡበት መንገድ ስፖርታዊ ጨዋነት የጎደለውና ሊታረም የሚገባው ነው።
ትናንት በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ሌላ ጨዋታ መከላከያ ፌዴራል ማረሚያ ቤቶችን 26 ለ 20 በሆነ ውጤት ሲያሸንፍ ቡታጅራ ላይ ፌዴራል ፖሊስ ቡታጅራ ከተማን 26 ለ 17 አሸንፏል።
ከትናንት በስቲያ ዱራሜ ላይ መቐለ ሰብዓ እንደርታ ከምባታ ዱራሜን 30 ለ 27 አሸንፏል።
በሰባተኛው ሳምንት የሊጉ መርሃ ግብር ጎንደር ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያላደረጉ አራፊ ክለቦች ናቸው።
በሌላ በኩል በሳምንቱ መጨረሻ ቀናት በኢትዮጵያ ሴቶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት በጎንደር ሁለት ጨዋታዎች ተካሂደዋል።
ትናንት ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ሀዋሳ ከተማን 62 ለ 34 በሆነ ሰፊ ውጤት ያሸነፈ ሲሆን ከትናንት በስቲያ ጎንደር ከተማ ሀዋሳ ከተማን 50 ለ 38 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በምድቡ በተደረገ ጨዋታ ጎንደር ከተማ ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽንን 86 ለ 78 በሆነ ውጤት ማሸነፉ ይታወሳል።
በተመሳሳይ በኢትዮጵያ ወንዶች ቅርጫት ኳስ ፕሪሚየር ሊግ በምድብ ሁለት ጎንደር ላይ ሁለት ጨዋታዎች የተካሄዱ ሲሆን ወልቂጤ ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 89 ለ 50 በሆነ ሰፊ ልዩነት አሸንፏል፤ ጎንደር ከተማም ወልቂጤ ከተማን 60 ለ 56 ረቷል።
ዓርብ የካቲት 15 ቀን 2011 ዓ.ም በምድቡ በተደረገ ጨዋታ ጎንደር ከተማ የካ ክፍለ ከተማን 66 ለ 43 በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር።
በኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን አዲስ የውድድር መርሃ ግብር መሠረት በወንዶችና በሴቶች ፕሪሚየር ሊግ በተመሳሳይ ምድብ በሁለት የተደለደሉት ሦስቱ ክለቦች ወደ ጎንደር አቅንተው ለሦስት ተከታታይ ቀናት ጨዋታቸውን አካሂደዋል።
በተጨማሪም ዛሬ በሀበሻ ሲሚንቶ የወንዶች ቮሊቦል ፕሪሚየር ሊግ 7ኛ ሳምንት መርሃ ግብር በአዲስ አበባ ትንሿ ሁለገብ ስታዲየም በተደረገ ጨዋታ አዲስ አበባ ፖሊስ አዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣንን በሦስት የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።