አብን የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር በትኩረት እሰራለሁ አለ - ኢዜአ አማርኛ
አብን የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠናከር በትኩረት እሰራለሁ አለ
አሶሳ የካቲት 17/2011 የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የኢትዮጵያ አንድነት ለማጠናከር በትኩረት እንደሚሰራ ምክትል ሊቀመንበሩ ገለጹ።
ንቅናቄው ዛሬ በአሶሳ ከተማ ከሚገኙ አባላቱና ደጋፊዎቹ ጋር ተወያይቷል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በለጠ ሞላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት ንቅናቄው ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ጎልብቶ እንዲወጣ ያለሰለሰ ጥረት ያደርጋል።
በአንዳንድ ወገኖች የሚሰነዘርበት ትችትም አግባብነት እንደሌለውም ገልጸዋል።
ንቅናቄው የትኛውንም ሕዝብ በጠላትነት ፈርጆ እንደማይንቀሳቀስ አስረድተዋል፡፡
“አሁን ጠንካራ ፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር የአማራን ህልውና እውን ካደረግን በኋላ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ወደ ዜግነት ፖለቲካ እንገባ ይሆናል”
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን)ምክትል ሊቀመንበሩ አቶ በለጠ ሞላ
“ለአማራ ሕዝብ ተደራጅቶ መታገል የህልውና ጉዳይ ነው” ያሉት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ባለፉት 27 ዓመታት ብሔሩ ላይ የደረሰው ግፍ ማብቃት አለበት ብለዋል፡፡
ከአማራ ክልል ውጪ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የብሔሩ ተወላጆች እንዳሉ የሚናገሩት አቶ በለጠ ፣ በክልላቸው በሠላም እንዳይኖር የሚፈልጉ አካላት ሆን ብለው በየአካባቢው ምክር ቤቶች ውክልና እንዳሳጡት አስረድተዋል፡፡
ይህ ሁኔታ ግን ከዚህ በኋላ መቀጠል እንደሌለበት አቶ በለጠ ይናገራሉ፡፡
“ባለፉት 10 ወራት በአገሪቱ የታየውን ለውጥ አብን ይደግፋል” ያሉት አቶ በለጠ የሕዝቦች እኩልነት፣ ሠላምና አንድነት የሠፈነባት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ይሠራል ብለዋል፡፡
ሰሞኑን በአንዳንድ አካባቢዎች ለውጡን የሚገዳደሩ አዝማሚያዎች መታየታቸውን የሚናገሩት ምክትል ሊቀመንበሩ፣ የለውጥ ኃይሉ ችግሩን ፈጥኖ እንዲያስተካክል አስገንዝበዋል፡፡
በውይይቱ ከተሳተፉት የንቅናቄው አባላት መካከል አቶ ጸዳል ዳምጤ እንዳሉት “ጠንካራ የአማራ የፖለቲካ ድርጅት አለመኖር በተለይም ከአማራ ክልል ውጪ ያሉ የብሔሩ ተወላጆች በርካታ በደሎች እንዲፈጸምባቸው ምክንያት ሆኗል፡፡”
“በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገኘው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የአማራ ሕዝብ የሚፈለገው በምርጫና በግብር ወቅት ብቻ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው፣ የብሔሩ ተወላጆች የሚፈልጉት ለሕዝቡ ጥቅም የሚቆም የፖለቲካ ፓርቲ ነው ብለዋል፡፡
“በአገሪቱ ለውጥ ስለመኖሩ እጠራጠራለሁ” የሚሉት እኚሁ አስተያየት ሰጪ፣ “አሁንም የአንድ ብሔር የበላይነት ተመልሶ እየመጣ ነው” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“የግለሰብ መብት ሲከበር የዜጎች መብት ይከበራል” የሚሉት ሌላው ተሳታፊ አቶ በየነ ዓለሙ ደግሞ ከአማራዴሞክራሲያዊ ፓርቲ(አዴፓ) ጋር ተቀራርቦ የመሥራት ስምምነታችሁን ምን ያህል ተግባራዊ ታደርጋላችሁ የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡
“አብን ከብሔር ይልቅ የዜግነት ፖለቲካ ቢከተል አይሻለውም ነበር ወይ? “ የሚል ጥያቄ ከሌሎች ተሳታፊዎች ለአብን አመራሮች ተነስቷል፡፡
ምክትል ሊቀመንበሩ በሰጡት ምላሽ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚደረሰውን በደል ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ውይይት በማድረግ እንደሚፈቱ አስታውቀዋል፡፡
በአብን አዴፓ መካከል መሠረታዊ ልዩነት ቢኖርም፤ለህዝቡ ጥቅም ሲባል ግን በጋራ ለመሥራት ዝግጁ ነን ብለዋል፡፡
“ይህ ማለት ግን አብን በአዴፓ ይጠቃለላል ማለት አይደለም ፤ ይልቁንም ሌሎች ፓርቲዎች ወደ አብን ይጠቃለላሉ እንጂ” ሲሉ አብራርተዋል፡፡
የዜግነት ፖለቲካ በኢትዮጵያ እንዲተገበር ፍላጎት ብቻ ሳይሆን፤ ጥረት ማድረጉን አመልክተዋል። በአገሪቱ ለዜግነት ፖለቲካ ምህዳር ባለመኖሩ ሳይሳካ መቅረቱን አስረድተዋል፡፡
አብን ወደ ብሔር ፖለቲካ ለመግባት የተገደደው በዚሁ ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
“አሁን ጠንካራ ፖለቲካ አደረጃጀት በመፍጠር የአማራን ህልውና እውን ካደረግን በኋላ ከሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር በመደራደር ወደ ዜግነት ፖለቲካ እንገባ ይሆናል” ሲሉም የፓርቲውን የወደፊት አቅጣጫ አመላክተዋል፡፡