በጎንደር ከተማ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም የሚያግዝ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ተካሄደ
ጎንደር የካቲት 17/2011 በጎንደርና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች መልሶ ለማቋቋም እንዲያግዝ ዛሬ በተዘጋጀ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን የድጋፍ አሰባሰቢ ኮሚቴው አስታወቀ፡፡
የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተመሰገን ሰጥአርገው እንደተናገሩት የተፈናቃይ ወገኖችን ችግር ለመፍታት አጋር መሆናችንን በተግባር ለማሳየት የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሙን ማዘጋጀት ችለዋል፡፡
" ይህ ድጋፍ ተጀመረ እንጂ በዚህ የሚያበቃ አይደለም" ያሉት ሰብሳቢው አሁን ከተገኘው የገንዘብ መጠን በላይ የሚሆን ገቢ በአይነትና በገንዘብ ለመሰብሰብ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል፡፡
ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የሚያደርገው ጥረት እንደሚደግፉና ለማቋቋም የተጀመረው ገንዘብ የማሰባሰብ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል፡፡
ነዋሪነታቸው በአዲስ አበባ የሆኑትና የጎንደር ከተማ ተወላጁ አቶ ኃብታሙ አዱኛ በበኩላቸው ከዚህ ቀደም ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውሰው በዛሬው ዝግጅትም ሀምሳ ሺህ ብር መለገሳቸውን ተናግረዋል፡፡
በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ የአማራና የቅማንት ህዝቦች ከቂምና ከቁርሾ በመውጣት ኢትዮጵያዊትን ይዘው መሻገር እንዳለባቸውም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በፕሮግራሙ ላይ የተገኘው አርቲስት ሻምበል በላይነህ ከቀረበው የሙዚቃ ዝግጅት በሽልማት የተበረከተለትን ዘጠኝ ሺህ ብር ለተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም እንዲያግዝ ለግሷል፡፡
የሰሜን ጎንደር ሀገረ-ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሃንስ " መላው የጎንደር ህዝብ ሰላሙንና አንድነቱን ጠብቆ ለፈጣሪው የሚቀርብ ስራ መስራት አለበት" ብለዋል፡፡
ሀገረ ስብከቱ 50ሺህ ብር መለገሱን ገልጸው በጎንደርና አካባቢው የሚገኙ ሁሉም አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እንደገቢያቸው መጠን ከ10 ሺህ እስክ 30 ሺህ ብር ድረስ ለመርዳት መወሰናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ተፈናቃዮች ለማቋቋም እንዲያግዝ ዛሬ በጎንደር ከተማ በተዘጋጀው የገቢ መሳበሳቢያ ፕሮግራም የተለያዩ ተቋማት፣ ግለሰቦች፣ባለሃብቶችና ወጣቶች ድጋፍ እንዳደረጉ ተገልጿል፡፡
በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ወቅት በአስተባባሪ ኮሚቴው በተከፈተ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ ማድረጊያ ቁጥር 1000274815926 በጎንደርና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ እርዳታ ሁሉም ኢትየጵያዊ ገቢ ማድረግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡