የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሂሩት ዘመነ ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር አደረጉ

አዲስ አበባ  የካቲት 17/2011 የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሂሩት ዘመነ በተማሩበት የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት ተገኝተው ለተማሪዎች የማነቃቂያ ንግግር አደረጉ።

ሚኒስትር ዴኤታዋ የዓለምን የስልጣኔ ምንጭ የሚዳስሱ፣ በኢትዮጵያውያን የተጻፉ የባህረ ሃሳብ መጽሕፍት እንዲሁም ፍቅርና መቻቻልን የሚያስተምሩ መጽሐፍትን ለትምህርት ቤቱ አበርክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከአርቲስቶች ጋር በነበራቸው ቆይታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናትና ታዋቂ ሰዎች ለተማሪዎች የህይወት ተሞክሯቸውን እንዲያጋሩ ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት ሚኒስትር ዴኤታዋ ተሞክሯቸውን ለተማሪዎች አጋርተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የስኬት መሰረት ከመምህራንና ከቤተሰብ ከሚገኘው እውቀት በተጨማሪ በማንበብ፣ ጥረት በማድረግና በእችላላሁ መንፈስ በመስራት ነው።

ተማሪ አድጎ ቤተሰቡንና አገሩን መጥቀም የሚችለው ዛሬ ላይ በእውቀትና በስነ ምግባር ታንጾ ሲያድግና ዓላማቸው ጥሩ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመተጋገዝ ዕውቀትና ልምድ ሲያዳብር ነው።

''ዛሬ ላይ መድረክ ላይ ወጥቼ ያለፍርሃት እንድናገር የቻልኩት በትምህርት ቤት ባዳበርኩት የስነጽሁፍ ውድድር፣ የቲያትር ትምህርት፣ የክርክርና የቤተሰብና የመምህራን ድጋፍ ነው'' ብለዋል።

''መምህራን አገራችንን እንድንወድ በስነምግባር ታንጽን እድናድግና የንባብ ባህላችን እንዲያድግ ትልቅ እገዛ ያደርጉልን ነበር'' ብለዋል።

መምህራን በቀጣይ አገርን ማገልገል ብዙ ዜጋን ለማፍራትና አንባቢ ትውልድን ለመፍጠር የግብረ-ገብና የሞራል ትምህርት በአግባቡ ማጠናከር እንዳለባቸው ጠቁመዋል።

ተማሪዎችም ከቤተሰብና ከመምህራንና ከሚያገኙት እውቀት በተጨማሪ በማንበብ፣ ጓደኛን በመውደድ፣ ከተንኮልና ከረብሻ በመራቅ የነገዋን ኢትዮጵያ እንዲረከቡ ጥሪ አቅርበዋል።

በትምህርት ቤቶች የሚሰጡት የግብረ-ገብና የሞራል ትምህርት አገር ተረካቢ ትውልድን ለመቅረጽ ከፍተኛ አተዋጽኦ ስላለው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ገልጸዋል።

ሚኒስትር ዴኤታዋ አሁን ያደረጉት የመጽሐፍት ስጦታ የህይወት መሰረት የሆናቸውና ሌሎች እንዲማሩባቸው በማሰብ ሲሆን በቀጣይ ለትምህርት ቤቱ ሌሎች መጽሐፍቶችን እንደሚያበረክቱ ቃል ገብተዋል።

በእለቱ የቀድሞና አሁን በመማርና ማስተማር ላይ ያሉ የተመረጡ መምህራንና ተማሪዎች የተገኙ ሲሆን የቀድሞዎቹ መምህራንና ተማሪዎች  የህይወት ተሞክሮዎችን ለተማሪዎች አቅርበዋል።

ከዚህ ቀደም የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ጥላዬ ጌቴ በተማሩበት ትምህርት ቤት ለተማሪዎች  የማነቃቂያ ንግግር ማድረጋቸው ይታወሳል።

የቅድስት ስላሴ ካቴድራል ትምህርት ቤት በ1955 ዓም  የተመሰረተ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ2 ሺህ 500 በተለይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በማስተማር ላይ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም