ድርጅቱ የሚያከናውነውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ድርጅቱ የሚያከናውነውን በጎ ተግባር አጠናክሮ እንደሚያስቀጥል ገለጸ
አዲስአበባ የካቲት 17/2011 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ምእመናን መታሰቢያ ድርጅት ለኢየሩሳሌም የሚያከናውነውን የበጎ አድራጎት ስራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለፀ።
ድርጅቱ የተመሰረተበትን 55ኛ ዓመት ዛሬ ሲያከብር የቤተክርስቲያኗ ብጹአን አባቶችና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።
በበአሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሊቀጳጳስ ብጹእ ወቅዱስ አቡነ መርቆሪዮስ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብፁእ ዶክተር አቡነ አረጋዊና የድርጅቱ አባላት ተገኝተዋል።
በኢየሩሳሌም የሚገኙ ታሪካዊ ይዞታዎች እንዲጠበቁ፣ የተወሰዱ ቅርሶች እንዲመለሱ እና በየዓመቱ ኢየሩሳሌምን ለመሳለም ለሚሄዱ ምእመናን የጉዞ ፕሮግራም ለማዘጋጀትና ለማስጎብኘት የተቋቋመው መታሰቢያ ድርጅቱ የበጎ አድራጎት ተግባራትን እንደሚፈጽም ተገልጿል።
በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ድጋፍ ለመስጠትና በዴርሱልጣን ገዳማት ላይ ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለመሻትና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር አብሮ እየሰራ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።
ድርጅቱ ሲቋቋም በ158 ሰዎች ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ አባላትን ማፍራቱ ታውቋል።
ድርጅቱ ከመንፈሳዊ ተግባሮች በተጨማሪ በተለያዩ በጎ ተግባራት ላይ በግንባር ቀደምትነት ሲሳተፍ የቆየ ሲሆን ይህንን ተግባሩን በቀጣይም እንደሚፈጽም ተነግሯል።
በአገሪቱ ለሚከናወኑ የልማት ስራዎች ድርጅቱ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ገልፀው በቅርቡም በአዲስ አበባ የጎዳና ተዳዳሪዎች ለማቋቋም ለሚደረገው እንቅስቃሴ ግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ ያሳያል።
የቤተክርስቲያኒቷ የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብፁእ ዶክተር አቡነ አረጋዊ ''ድርጅቱ 55 ዓመት ያስቆጠረና ትውልድ እየተቀባበለ ያስቀጠለው ሰናይ ተግባር የያዘ ነው'' ብለዋል።