በጋምቤላ ክልል በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ 69 ከመቶ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል በግማሽ ዓመቱ የተሰበሰበው ገቢ 69 ከመቶ ነው
ጋምቤላ የካቲት 17/2011 የጋምቤላ ክልል የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ባለመጠናከሩ በግማሽ ዓመቱ የሰበሰበው 69 ከመቶ መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ኡሞድ ኡዋር ለኢዜአ እንደገለጹት ቢሮው ባለፉት ሰድስት ወራት ለመሰብሰብ ካቀደው 373 ሚሊዮን ብር ያሳካው 258 ሚሊዮን ብር ነው።
ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃጸር የ54 ሚሊዮን ብልጫ ያለው ቢሆንም ፤ክንውኑ ከዕቅዱ ያነሰ መሆኑን ተናግረዋል።
ዕቅዱ ያልተሳካው በማስፈጸም አቅም ውስንነት፣የአመራር አካላት ለዘርፉ ትኩረት ባለመስጠታቸውና በግብር ከፋዮች የግንዛቤ ማነስ ነው ብለዋል።
እንዲሁም በወረዳዎችና በሴክተር መሥሪያ ቤቶች የሚሰበሰበው ገቢ ለብክነት መዳረግና የተጨማሪ እሴት ታክስ(ቫት) ተመዝጋቢዎች ደረሰኝ ያለመቁረጥ ሌሎቹ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቢሮው በቀጣይ ግማሽ በጀት ዓመት በዘርፉ ያሉትን ችግሮችንና የሰው ኃይል አደረጃጀቱን በማስተካከል የተሻለ ገቢ ለመሰብሰበ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የክልሉ ገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጋትዊች ኩን እንዳሉት የክልሉ የገቢ አሰባሰብ ሥርዓት ባለመጠናከሩ በየዓመቱ ለበጀት እጥረት እየተዳረገ ነው ብለዋል።
ክልሉ ከፍተኛ የገቢ አቅም ያለው ቢሆንም የአሰባሰብ ሥርዓቱ ዘመናዊ ባለመሆኑ የካፒታልና የመደበኛ በጀት እጥረት እያጋጠመ መሆኑን አስታውቀዋል።
ስለሆነም የክልሉን የገቢ አቅም ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በትኩረትና በቅንጅት እንዲሰሩ ምክትል ኃላፊው ጠይቀዋል ።
በክልሉ በተያዘው በጀት ዓመት 750 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ታቅዷል።