የፋሲል ከተማና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ - ኢዜአ አማርኛ
የፋሲል ከተማና የድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቀቀ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 በዝናብ ምክንያት ዛሬ እንዲካሄድ የተደረገው የ24ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ መርሃ-ግብር የፋሲል ከተማና ድሬዳዋ ከተማ ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተጠናቋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባወጣው መርሃ-ግብር ቡድኖቹ ትናንት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ማካሄድ የነበረባቸው ቢሆንም በጎንደር በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጨዋታው ተራዝሞ ዛሬ ጠዋት ረፋድ ላይ እንዲካሄድ ተወስኖ ነበር። በዚሁ መሰረት ሁለቱ ቡድኖች ዛሬ በአጼ ፋሲለደስ ስታዲየም ባደረጉት ጨዋታ ግብ አልተስተናገደም። ፋሲል ከተማ ነጥቡን ወደ 34 ከፍ በማድረግ ስድስተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን በአንጻሩ ድሬዳዋ ከተማ ነጥቡን ወደ 26 ከፍ በማድረግ 12ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። አንድ ጨዋታ በተፈጥሯዊ ክስተቶች ሳይካሄድ ቢቀርና ቢቋረጥ ጨዋታው በቀጣዩ ቀን እንዲካሄድ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ የውድድር መመሪያ ያዛል። የ24ኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ መርሃ-ግብር የመጨረሻ ጨዋታ ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ከቀኑ 11 ሰዓት ኢትዮጵያ ቡናና ደደቢት ይገናኛሉ። የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በስፖርት አፍቃሪው ዘንድ በጉጉት ይጠበቃል። የፕሪሚየር ሊጉን የመጀመሪያ ዙር በመሪነት በማጠናቀቅ ጥሩ የዋንጫ ግስጋሴ አሳይቶ የነበረው ደደቢት በሁለተኛው ዙር ካደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ በማሸነፍ ያሳየው ደካማ ጅማሬ ከዋንጫው ተፎካካሪዎች በነጥብ እንዲርቅ አድርጎታል። የዛሬው ጨዋታ ለደደቢት ወደ መሪዎቹ ለመጠጋትና ወደ ዋንጫ ፉክክሩ ለመመለስ እጅግ ወሳኝ ነው። ደደቢት በ33 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በአንጻሩ ኢትዮጵያ ቡና በሁለተኛው ዙር መልካም ጅማሮን አሳይቷል። ባደረጋቸው ስድስት ጨዋታዎች ሶስት አሸንፎ፣ ሁለት ተሸንፎ አንድ አቻ ወጥቷል። በአሁኑ ወቅትም 36 ነጥብ በመሰብሰብ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን የዛሬውን ጨዋታ ካሸነፈ ከመሪዎቹ ጋር ያለውን የነጥብ ልዩነት ማጥበብ ይችላል። ይህን ጨዋታ ፌዴራል ዳኛ ማኑኤ ወልደፃዲቅ በመሐል ዳኝነት ይመሩታል። ትናንት በፕሪሚየር ሊጉ በተደረጉ ጨዋታዎች መቀሌ ከተማ ሃዋሳ ከተማን እንዲሁም ሲዳማ ቡና አዳማ ከተማን በተመሳሳይ አንድ ለዜሮ ሲያሸንፉ አርባ ምንጭ ከተማ ወልዲያ ከተማን አምስት ለዜሮ በሆነ ሰፊ የግብ ልዩነት ማሸነፍ ችሏል። ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ከጅማ አባ ጅፋር እንዲሁም መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ሲያጠናቅቁ ኢትዮ ኤሌትሪክና ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ መጠናቀቁ የሚታወስ ነው። የፕሪሚየር ሊጉን የደረጃ ሰንጠረዥ መቀሌ ከተማ በ42 ነጥብ ሲመራ፣ ጅማ አባ ጅፋርና ቅዱስ ጊዮርጊስ በተመሳሳይ 41 ነጥብ በግብ ክፍያ ተበላልጠው በቅደም ተከተል ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል። ኢትዮ ኤሌክ ትሪክ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲና ወልዲያ ከተማ በቅደም ተከተል ከ14 እስከ 16 ያለውን ደረጃ በመያዝ ወራጅ ቀጠና ውስጥ ይገኛሉ። የሊጉን ኮከብ ግብ አግቢነት ናይጄሪያዊው የጅማ አባጅፋር ተጫዋች ኦኪኪ አፎላቢ በ15 ግቦች ሲመራ፣ የደደቢቱ ጌታነህ ከበደና ጋናዊው የኢትዮ ኤሌትሪክ ተጫዋች አልሃሰን ካሉሻ በተመሳሳይ 10 ግቦች ይከተላሉ።