የሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ማንጎን በማዳቀል ምርትና ምረታማነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የሸዋሮቢት ማረሚያ ቤት ማንጎን በማዳቀል ምርትና ምረታማነትን እያሳደገ ነው
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 የሸዋሮቢት የተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት የማንጎ አትክልትን ጥራትና ምርታማነት በማሳደግ ረገድ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ገለጸ፡፡ በዘርፉ ብቁ የሰው ኃይል እጥረት እንደገጠመውም ገልጿል፡፡ በማረሚያ ቤቱ የልማትና ማቋቋም ቡድን መሪ ሰርጀንት ጥዑማይ ግርማይ እንደገለጹት ማረሚያ ቤቱ የማንጎን ምርታማነትና ጥራት ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ለዚህም መደበኛውን ማንጎ ከአፕል ማንጎ ጋር በማዳቀል ጥራትና ምረታማነቱን ማሻሻሉን በአብነት ጠቅሰዋል፡፡ ማረሚያ ቤቱ የተዳቀሉ የማንጎ ዝርያዎችን ከራሱ በተጨማሪ ለአካባቢው አርሶ አደሮች ችግኝ እያከፋፋለና ገበያ እያረጋጋ መሆኑንም አመልክተዋል። የተዳቀለው አፕል ማንጎ በሄክታር 80 ኩንታል ምርት የሚያስገኝ ሲሆን ይህም በሄክታር የ40 ኩንታል ጭማሪ እንደታየበት ነው የተናገሩት፡፡ ይሁንና ማረሚያ ቤቱ በዘርፉ የሰለጠነ የባለሙያ እጥረት ችግር ለግብርና ስራው እንቅፋት እንደሆነበት ነው ያመለከቱት። የማረሚያ ቤቱ አስተዳዳር ዋና ሱፐር ኢንተንዳንት የማነ አስፋው በበኩላቸው የባለሙያ እጥረት እንዳለበት ገልጸው፤ ይህም ከስፍራው በረሃማነትና ከደመወዝ ጋር የተያያዘ እንደሆነ ተናግረዋል። የከተማዋ ምክትል ከንቲባ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ፀሐዬ አስናቀ እንዳሉት ማረሚያ ቤቱ በሚያከናውነው የግብርና ስራ ለሸዋሮቢት ከተማና አካባቢዋ ህይወት መሰረት ሆኗል፡፡ ማረሚያ ቤቱ በበጀት ዓመቱ ከግብርና ልማት ስራዎቹ 7 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር ለመሰብሰብ አቅዶ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ 5 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ገቢ ሰብስቧል፡፡ ሰፊ የመስኖ ልማት ባለቤት የሆነው የሸዋሮቢት ተሃድሶ ልማት ማዕከል ማረሚያ ቤት በተያዘው የምርት ዘመን ከ133 ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ቋሚ አትክልቶችና ልዩ ልዩ ሰብሎች ሸፍኗል፡፡