ቀጥታ፡

የኦነግ ታጋዮች አቀባበል እየተደረገላቸው ነው

ነቀምቴ የካቲት 17/2011 የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጋዮች ወደ ተዘጋጀላቸው ጣቢያዎች ሲደረሱ ህዝቡ ደማቅ አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን የአባ ገዳዎች ህብረት ቴክኒክ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

የኮሚቴው አባልና የአባገዳዎች ሕብረት ሰብሰቢ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ለኢዜአ እንዳተናገሩት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር ታጋዮች ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ተዘጋጀላቸው ማዕከል እየገቡ ያሉት ቀደም ሲል መንግስትና ኦነግ በደረሱት ስምምነት መሠረት ነው ፡፡

ታጋዮቹ በምዕራብ ኦሮሚያ  በተዘጋጀላቸው  ግዳሚ፣ደምቢ ዶሎ፣ እና ቃቄ ከተሞች በሚገኙ ጣቢያዎች ቀርበው ትጥቃቸውን ለአባገዳዎች እያሰረከቡ ሲገቡ የአካባቢው ህዝብ ደስታውን በመግለጽ ደማቅ አቀባባል እያደረገላቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ታጋዮቹ ካሉበት የቦታ ርቀትና የመገናኛ ችግር አንፃር ለመምጣት ፍላጎት እያላቸው አሁንም ያልደረሱ  መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡

በአጭር ጊዜ ውስጥም  በቄለም ወለጋ ዞን በኩል  138 የኦነግ ታጋዮች  ወደ ሰላማዊ ህይወት መመለስ መመቻላቸው ትልቅ ስኬት መሆኑን አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ ገልጸዋል፡፡

በተላለፋላቸው ጥሪ መሰረት የቀሩትም እንዲመጡ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአባ ገዳዎች ህብረት የቴክኒክ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበርና የሚዲያ ኮሚቴ አባል አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው  ከ220 የሚበልጡ  የኦነግ ታጋዮች በምዕራብ ወለጋ ዞን ወደ ተዘጋጀላቸው ጣቢያዎች ሲደርሱ ህዝቡ አቀባበል እያደረገላቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ለታጋዮቹ የተዘጋጁላቸው ጣቢያዎች  መንዲ፣ነጆ፣ቤጊ፣እና ጉሊሶ አካባቢዎች መሆኑን አመልክተዋል፡፡

አቶ በቀለ ገርባ እንዳሉት በየጣቢዎቹ ቀርበው ትጥቃቸውን ለአባገዳዎች ያስረከቡት ታጋዮቹ  በትግሉ ሜዳ ለዓመታት የቆዩ ናቸው፡፡

መንግስትና ኦነግ በደረሱት ስምምነት  መሰረት የቀረበላቸውን ጥሪ ተቀብለው ትጥቃቸውን በማስረከም ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመምጣት መወሰናቸው ለአባገዳዎች ጭምር ያላቸውን አክብሮት የሚያሳይና ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀሩትም ይህንን ዕድል በመጠቀም እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በግዳሚ ከተማ የቀበሌ አንድ ነዋሪ አቶ ሳሙኤል ወንድሙ በሰጡት አስተያየት ታታጋዮቹ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የቀረባላቸውን ጥሪ በመቀበል ከህብረተሰቡ ጋር መቀላቀላቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡

ታጋዮቹ  ትጥቃቸውን ፈትተው ወደ ሰላማዊ ኑሮ መምጣታቸው ለሰላም   መስፈን ትልቅ አስተዋጽኦ ያለውና የኦሮሞን ሕዝብ ያስደሰተ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አቶ ሰለሞን ገመቹ ናቸው፡፡

ከታጋዮቹ መካከል  ሞላሌ ጎንጄ በሰጠው አስተያየት ወደ ትጥቅ ትግሉ የተቀላለቀለው ምዕራብ ወለጋ ዞን ቤጊ ወረዳ በ1982 ዓ.ም. እንደሆነ ተናግሯል፡፡

የዳውድ ኢብሳና የአባገዳዎችን ጥሪ ተቀበሎ መምጣቱን  ገልፆ በሰላማዊ መንገድ ለመታገል ዝግጁ መሆኑንና የቀሩትም ታጋዮች ጊዜ ተሰጥቷቸው ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመጡ ማድረግ  እንደሚገባም አመልክቷል፡፡

ሌላው ታጋይ ያሲን አብዱልቃድር በበኩሉ በመሣሪያ ኃይል የሚመጣ ለውጥ ባለመኖሩ በቀረበላቸው ጥሪ መሰረት  ትጥቃቸውን ለአባገዳዎች አስረክበው ሰላማዊ ትግል መምረጣቸውን ገልጿል፡፡

በጫካ የቀሩ ሌሎች ወንድሞችም ወደ ሰላማዊ ኑሮ እንዲመጡ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም