የኦሮሞ ህዝብ በሀገር ሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ላይ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ተመለከተ

62

አዳማ የካቲት 17/2011 የኦሮሞ ህዝብ በአካባቢውን ብሎም  በሀገሩ ሰላምና ዴሞክራሲያዊ አንድነት ግንባታ ላይ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት የክልሉ  ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳ አመለከቱ፡፡

ፕሬዝደንቱ በአዳማ ከተማ እየተካሄደ ባለው የሞዴል አርሶ አደሮች የሽልማት ስነ-ስርዓት ሂደት እንዳሉት ህዝቡ ያገኘውን ፖለቲካዊ ድልና ነጻነት በልማት መስኮች በመድገም እራሱን ከድህነት ማላቀቅ  አለበት፡፡

የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ሰላም ለመጠበቅና  ለውጡን ለማስቀጠል የኦሮሞ ህዝብ አንድነቱን ለማጠናከር የድርሻውን መወጣት እንደሚገባው አመልክተዋል።

" በክልሉ ካሉ ሌሎች ብሔር ብሔረሰብና ህዝቦች ጋር በመሆን ዴሞክራሲያዊ አንድነት ከማጠናከር ጎን ህዝቡ አስተማማኝ ዲሞክራሲያዊ  ስርዓት እንዲገነባ መረባረብ ይጠበቅብናል" ብለዋል።

በየቦታው የሚሰነዘሩ የትንኮሳና የግጭት አስተሳሰቦችን ወደ ጎን በመተው ህዝቡ በትእግስትና በሆደ ሰፊነት የተጀመረውን ለውጥ ለውጤት እንዲበቃ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርግ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

የክልሉ ወጣቶችና ቄሮዎች ከሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች ጋር በመሆን  አስተማማኝ ሰላም እንዲረጋገጥና የህግ የበላይነት እንዲሰፍን እጅ ለእጅ ተያይዘው በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ  አቶ ለማ  አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም