የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ተጀመረ
አዲስ አበባ ግንቦት 21/2010 ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች የሚሳተፉበት የኢትዮጵያ የጠረጴዛ ቴኒስ ሻምፒዮና ዛሬ በኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት አካዳሚ ተጀመረ። እስከ እሁድ ግንቦት 26 ቀን 2010 ዓም በሚቆየው ሻምፒዮና ከሐረሪ፣ ኦሮሚያ፣ ትግራይና አፋር ክልሎች እንዲሁም ከድሬዳዋ አስተዳደር የተወጣጡ 39 ተወዳዳሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል። በሻምፒዮናው የሶማሌ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ አማራ፣ ጋምቤላና ደቡብ ክልሎች እንዲሳተፉ ጥሪ ቢቀርብላቸውም "በጀት የለንም" በሚል ምክንያት ከውድድሩ መውጣታቸውን የኢትዮጵያ ጠረጴዛ ቴኒስ ፌዴሬሽን የጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ አበባ አማረ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በበኩሉ በሻምፒዮናው ላይ የክለብ ተጫዋቾችን ማሳተፍ እንዲፈቀድለት ጥያቄ አቅርቦ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከውድድሩ ወጥቷል። ወይዘሮ አበባ እንዳሉት የከተማ አስተዳደሩ ክለብ ያቀረበው ጥያቄ ውድቅ የተደረገው በፌዴሬሽኑ ህገ-ደንብ መሰረት በአገር አቀፍ ውድድር ላይ የክለብ ተጫዋቾችን ማሳተፍ የማይቻል በመሆኑ ነው። ተተኪ ስፖርተኞችን ማፍራት፣ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያላቸውን አቅም እንዲፈትሹና በአህጉር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን ወክለው የሚሳተፉ ተወዳዳሪዎችን ለመምረጥ ሻምፒዮናው የበኩሉን ሚና ይጫወታል ተብሎ እንደሚታመን ኃላፊዋ ገልፀዋል። የሻምፒዮናው ተወዳዳሪዎች በሁለቱም ጾታዎች የነጠላ፣ ድብልቅ(ወንድና ሴት)፣ ጥንድ(ወንድና ወንድ ) የቡድን የዙር ውድድር እና የግል የበላይነት በሚሉ ዘርፎች ይሳተፋሉ። በእያንዳንዱ ዘርፍ አሸናፊ ለሚሆኑ ተሳታፊዎችም የዋንጫና የሜዳሊያ ሽልማት ተዘጋጅቷል።