ታዋቂ ግለሰቦችና አክቲቪስቶች ማህበራዊ ሚዲያን በኃላፊነት ሊጠቀሙበት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
ታዋቂ ግለሰቦችና አክቲቪስቶች ማህበራዊ ሚዲያን በኃላፊነት ሊጠቀሙበት ይገባል
አዲስ አበባ የካቲት 16/2011 ታዋቂ ግለሰቦችና አክቲቪስቶች ማህበራዊ ሚዲያን በሰከነና በኃላፊነት ስሜት ሊጠቀሙበት እንደሚገባ ተጠቆመ።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ፕሮጀክት ከካናዳ ኢምባሲ ጋር በመተባበር በጥላቻ ንግግር ዙሪያ ያዘጋጀው ውይይት ተካሂዷል።
በውይይቱ ላይ የህግ ምሁራን፣ የመብት ተሟጋቾችና ተጋባዥ እንግዶች የተሳተፉ ሲሆን የጥላቻ ንግግር ምንድነው?፣ የትኛው ንግግር ነው የጥላቻ የሚባለው?፣ መለያ ባህሪያቱ ምንድን ናቸው፣ መፍትሄውስ ምንድነው? በሚሉ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው።
በኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ ዘር፣ ሃይማኖትና ጾታን ጨምሮ ቡድንና ማህበራዊ አመጣጥን መሰረት ያደረጉ የጥላቻ ንግግሮች እየተበራከቱ ነው።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህር ዶክተር መሰንበት አሰፋ ባቀረቡት የውይይት መነሻ ጸሁፍ እንዳሉት የፖለቲካ መሪዎችና የመብት ተሟጋቾች በማህበረሰቡ ውስጥ ልዩነትን ከሚያሰፋ አጠቃቀም ሊቆጠቡ ይገባል።
በአገሪቷ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቢኖርም የጥላቻ ህግ ንግግር ምን ድረስ ያስቀጣል የሚለው ወሰን እንዳልተቀመጠለት ገልጸው በዚህ ላይ ልዩ ህግ ማውጣት እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
የውይይቱ ተሳታፊ ብርሃነመስቀል ቀለመወርቅ በበኩሉ በአገሪቷ ህዝቡ ሀሳቡን በነጻ የሚገልጽበት መገናኛ ብዙሃን አለመኖር ወደ ማህበራዊ ሚዲያ እንዲያዘነብል አድርጓል ሲል ተደምጧል።
እንደ ወጣቱ ገለጻ ህዝቡ በነጻ ሀሳቡን የሚገልጽበትና መገናኛ ብዙሃንና ጋዜጦች ማብዛት የጥላቻ ንግግርን ለመቀነስ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።
'ማህበራዊ ሚዲያውን ስንጠቀም በእውቀትና በማስተዋል ሊሆን ይገባል' ያለው ደግሞ ወጣት ቴዎድሮስ ፋንታ ነው።
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለጥላቻ ንግግር መፍትሄ ያሏቸውን ሀሳቦችም ሰንዝረዋል።
ስለ ጥላቻ ንግግር በስርዓተ ትምህርት የታገዘ ትምህርት በመስጠት ትውልዱን ማነጽ፣ ሀሰተኛ መረጃዎችና የውሸት ዜናዎችን መለየት መቻልና ገለልተኛ የሚዲያ ተቋማትን መፍጠር ከመፍትሄዎች መካከል ተጠቅሰዋል።
በማህበራዊ ሚዲያ ለሚነዙ የጥላቻ ንግግሮች ትኩረት አለመስጠት እንዲሁም የአጠቃቀም እውቀትን ማሳደግ ከተነሱ የመፍትሄ ሀሳቦች መካከል ናቸው።