ቀጥታ፡

አዲሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ታሪፍ ለከፍተኛ ክፍያ ዳርጎናል----የሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች

ሚዛን የካቲት 16/2011 አዲሱ የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ ታሪፍ ከጠበቅነው በላይ ለከፍተኛ ወጪ ዳርጎናል ሲሉ በሚዛን አማን ከተማ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በበኩሉ የታሪፍ ማሻሻያውን ተከትሎ ደንበኞች የተጠቀሙበትን ውዝፍ ሒሳብ አንድ ላይ እንዲከፈሉ መደረጉን በመግለፅ በሚቀርቡ ቅሬታዎች መሰረት ውዝፍ ሒሳቡ ተከፋፍሎ የሚከፈልበት አሰራር መዘርጋቱን አስታውቋል።

በከተማው አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡት መካከል የሕብረት ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ዘውዲቱ ወልደማርያም እንደገለፁት በአዲሱ ታሪፍ የጥር ወር 2011 ዓ.ም የተጠየቁት ክፍያ ፈፅሞ እንዳልጠበቁት ተናግረዋል ።

"ከዚህ ቀደም በየወሩ ለምጠቀምበት ኤሌክትሪክ ፍጆታ እስከ 28 ብር እከፍል ነበር፤ የጥር ወር 1ሺህ 183 ብር እንድከፍል ተጠይቄያለሁ" ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል ።

ወትሮውን ለመብራት ከሚጠቀሙት አምፖል በስተቀር በኤሌክትሪክ አጠቃቀማቸው ላይ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ እጅግ የተጋነነ ክፍያ መጠየቃቸው አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል ።

"በጥር ወር 2011 ዓ.ም ከኤሌክትሪክ አገልግሎት የመጣልኝ የሒሳብ ደረሰኝ በእጅጉ የተጋነነ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ዳኛቸው ጴጥሮስ ናቸው፡፡

ከዚህ ቀደም ለተጠቀሙበት የኤሌክትሪክ ኃይል ይከፍሉት የነበረው ወርሀዊ ገንዘብ ከ60 እስከ 70 ብር እንደነበር ያስታወሱት አቶ ዳኛቸው ባለፈው ወር 1ሺህ 200 ብር ክፍያ መጠየቃቸውን ገልፀዋል ።

በተቋሙ በኩል እንደ ወትሮው ሁሉ የኤሌክትሪክ መቆራረጥ መኖሩን ጠቁመው "የአገልግሎት ማሻሻያ ሳይደረግ በእኔም የፈጆታ አጠቃቀም ለውጥ ሳይኖር እጅግ የተጋነነ ክፍያ መጠየቁ  ቅሬታ ፈጥሮብኛል" ብለዋል ።

አቶ ምስክር ገረመው የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው "ባለፈው ወር የተጠየኩት ክፍያ ከተጠቀምኩበት ፍጆታ ጋር ፈጽሞ የተጣጣመ አይደለም " ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል ።

በወሩ የመጣላቸው የሒሳብ ቢል 3ሺህ 400ብር ክፍያ የያዘ በመሆኑ በባለሙያ እንዲፈተሽላቸው ለተቋሙ ማመልከታቸውን ተናግረዋል ።

የክፍያ ታሪፉ በዚህ ደረጃ መጨመሩ ተገልጋዩን ለከፋ ኢኮኖሚያዊ ጫና የሚዳርግ በመሆኑ ተቋሙ አሰራሩን ሊያሻሻል እንደሚገባ ነዋሪዎቹ ጠይቀዋል ።

በቦንጋ ዲስትሪክት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪ አገልግሎት የሚዛን ደኝበኞች አገልግሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ አስቻለው ታምሩ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ ከታህሳስ 30 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ የክፍያ ታሪፍ ማሻሻያ ተደርጓል ።

በተደረገው የክፍያ ማሻሻያ መሰረት ከ51 እስከ 100 ኪሎ ዋት 0.3564 ሣንቲም ሲከፈልበት የነበረው ታሪፍ ወደ 0.4591 ሣንቲም ማደጉን ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ከ101 እስከ 200 ኪሎ ዋት ላለው ከ0.49 ወደ 0.78 ሣንቲም ከፍ ማለቱን የገለጹት አቶ አስቻለው "የኤሌክትሪክ አጠቃቀም ፍጆታ በጨመረ ጊዜ ደግሞ የክፍያው መጠንም ያድጋል" ብለዋል፡፡

በተቋሙ ችግር ምክንያት ለሚቀርብ ቀሪ የውዝፍ ክፍያ ቅሬታዎቹን በመለየት የማስተካከያ ሥራ እንደሚከናወንም አቶ አስቻለው ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኮሚዩኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ያዕቆብ ታሪኩ በበኩላቸው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ህብረተሰቡ ተመሳሳይ ቅሬታ እያነሳ መሆኑን ተናግረዋል ።

አቶ ያዕቆብ እንዳሉት የታሪፍ ማስተካከያው የተሻለ አገልግሎት ለመስጠትና የአቅም ውስንነትን ለመቅረፍ ታስቦ የተደረገ ነው።

አዲሱ የክፍያ ታሪፍ ሲጀመር ደንበኞች ከዚህ ቀደም በቆጣሪቸው ላይ ያለውን ንባብ በሙሉ ጨርሰው እንዲከፍሉ በመደረጉ የክፍያ መጠኑ መጨመሩን አስረደተዋል ።

ይህንኑ ተከትሎ ከደንበኞች ለሚነሱ ቅሬታዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ፍኖተ ካርታ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል፡፡

ፍኖተ ካርታው ደምበኛው የመጣበትን ውዝፍ ክፍያ በተለያየ ጊዜ ቆራርጦ መክፈል የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሕብረተሰቡ የኤሌክትሪክ ኃይሉን በተገቢው ለመጠቀም በክፍያ ደረሰኙ ላይ የተቀመጡና የተመረጡ መጠቀሚያ ሰዓቶችን አውቆ እንዲገለገልም አቶ ያዕቆብ መልዕክት አስተላልፈዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም