በህዝብና ቤቶች ቆጠራ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በህዝብና ቤቶች ቆጠራ ትክክለኛ መረጃ ለማግኘት ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተጠቆመ
ጎንደር የካቲት 16/2011 በአራተኛው ሀገር አቀፉ የህዝብና ቤቶች ቆጠራ ትክክለኛውን መረጃ ለማግኘት የሁሉም እገዛ ያስፈልጋል ሲሉ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የስነ ህዝብ ምሁራን ገለጹ፡፡
የህዝብና ቤት ቆጠራ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ፋይዳው የላቀ መሆኑን ምሁራኑ ተናግረዋል።
በዩኒቨርሲቲው የስነ-ህዝብ ትምህርት ጥናት ክፍል ኃላፊ አቶ ብስራት ወርቁ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለፁት በስነህዝብና ቤቶች ቆጠራ ትክከለኛ መረጃ ለማግኘት በእውቀት ላይ የተመሰረተ ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል።
የኢኮኖሚ እቅዶችን ለማዘጋጀትም ሆነ ክልሎች ፍትሃዊ የሆነ የበጀት ድልድል እንዲኖራቸው አስተዋጾው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል ።
በፖለቲካው ዘርፍም ህዝቡ በፓርላማና በክልል ምክር ቤቶች ትክክለኛ የህዝብ ስልጣን የውክልና መቀመጫ እንዲያገኝ በማድረግ በኩል ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅሰዋል ።
በዩኒቨርሲቲው የስነ-ህዝብ ጥናት ትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር አጸደ ደስታ በበኩላቸው ቆጠራው የወደፊቱን የህዝብ ቁጥር ታሳቢ ያደረገ የመሰረተ ልማት እቅዶችን ለማዘጋጀትና ለመተግበር ይጠቅማል" ብለዋል ።
"ቆጠራው በአግባቡ ከተተገበረ ለፖሊሲ አውጪዎች ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመረጃ ላይ የተደገፈ ሳይንሳዊ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን እንዲያከናውኑ ያግዛል” ብለዋል፡፡
“የቀደመው የህዝብና ቤት ቆጠራ ክንውን ውጤት ከእንከን የጸዳ አልነበረም” ያሉት ዶክተር አጸደ ለ4ኛ ጊዜ በሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ እነዚህ ግድፈቶች እንዳይደገሙ በጥንቃቄ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
የጸጥታ ችግር ባለባቸውና የማንነት ጥያቄ በሚነሳባቸው አካባቢዎችም ቢሆን ቆጠራው ፍትሃዊና ግልጽነት በተላበሰ መንገድ ብቃት ባላቸው የቆጠራ ባለሙያዎች ሊካሄድ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡
ትክክለኛ ቆጠራ መካሄዱ የህዝቡን የማህበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎች በአግባቡ ለመመለስ የሚኖረውን ጠቀሜታ በመገንዘብ ሁሉም ህብረተሰብ በተለይ በተማረው ኃይል በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።
የጎንደር ዩንቨርሲቲ በስነ-ህዝብ ሙያ የበቁ ተማሪዎችን አሰልጥኖ እያስመረቀ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶክተር አጸደ ኤጀንሲው እነዚህን ምሩቃን በስፋት ሊጠቀምባቸው እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በተቋሙ የማህበራዊ ሳይንስና ስነ-ሰብ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ካሳሁን ተገኘ በበኩላቸው እንዳሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የህዝብና ቤት ቆጠራውን በእውቀት በመደገፍ የህዝቡን ግንዛቤ የማሳደግ ሃገራዊ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
የጎንደር ዩንቨርሲቲም ለቆጠራው ስኬታማነት የምሁራን ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ገልጸው ህዝቡም ቆጠራው የሚያስገኘውን ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ ፋይዳ በመገንዘብ ትክክለኛ መረጃ በመስጠት ሊሳተፍ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
“በህዝብና ቤት ቆጠራ ሥራው የመረጃ አሰባሰብ ስርአቱ በቴክኖሎጂ መደገፉ የቆጠራውን ውጤት ተአማኒ ከማድረጉም በላይ መረጃውን ለመሰብሰብ የሚፈጀውን ጊዜ በማሳጠር ውጤቱን በአጭር ጊዜ ይፋ ለማድረግ አስተዋጽኦ ይኖረዋል” ብለዋል።
በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ስታስቲክስ ኤጀንሲ የጎንደር ቅርንጫፍ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ጎንደር ከተማን ጨምሮ በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምዕራብና በማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች መጋቢት 30 ለሚካሄደው የህዝብና ቤት ቆጠራ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡
በዞኖቹ 11 የቆጠራ ማስተባባሪያ ማዕከላት የተቋቋሙ ሲሆን 10ሺህ 500 የሚሆኑ ቆጣሪዎችና አስተባባሪዎች ተመልምለው ስልጠና ለመስጠት እየተመቻቸ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡